ህወሓት እየፈጸመ ያለው ትውልድ የማጥፋት ዘመቻ የኢትዮጵያ ህጻናትን ልብ እየሰበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ህወሓት እየፈጸመ ያለው ትውልድ የማጥፋት ዘመቻ የኢትዮጵያ ህጻናትን ልብ እየሰበረ ነው
አርባ ምንጭ፣ ሐምሌ 22/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሐት ህጻናትን ለጦርነት በማሰለፍ እየፈጸመ ያለው ትውልድ የማጥፋት ዘመቻ የኢትዮጵያ ህጻናትን ልብ እየሰበረ ነው።
ድርጊቱ ያሳዘናቸውና ያሳሰባቸው የደቡብ ክልል እንዲሁም በክልሉ የጌዴኦ ዞንና የኮንሶ ህጻናት ፓርላማ አባላት አሸባሪው ህወሐት ህጻናትን ለጦርነት እያሰለፈ ያለውን ተግባር ሰሞኑን ማውገዛቸው ይታወሳል።
ዛሬ ደግሞ በክልሉ የጋሞ ዞን ህጻናት ፓርላማ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ድርጊቱን እንዲያወግዝና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ኢ-ሰብአዊ ተግባሩን ባፋጣኝ እንዲያስቆም ጠይቋል።
የፓርላማው አባላት በትግራይ ህጻናት በትከሻቸው የጦር መሳሪያ በማንገብ በጦር ግንባር ተሰልፈው የሚማገዱበት ሁኔታ እንዳሳዘናቸውና ልባቸውን የሰበረ በመሆኑ ዓለማቀፍ ማህበረሰብ ድርጊቱን እንዲያወግዝ ጠይቀዋል።
የፓርላማው ምክትል አፈ-ጉባዔ ህፃን ሜሮን ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጸችው አሸባሪው ህወሃት ህፃናትን በጦርነት በመማገድ ትውልድ የማጥፋት ዘመቻ እየፈጸመ ይገኛል።
ጥበቃና ከለላ ሊደረግላቸው የሚገባ ሀገር ተረካቢ ህፃናት ጠብመንጃ አንግበው በጦር ግንባር እንዲሰለፉ መገደዳቸው የስነ ልቦና ችግር ውስጥ እንደከተታት ገልጻለች።
"ህፃናቱ የቤተሰብ ጥበቃና ክትትል ሊደረግላቸው ሲገባ ህወሓት በአንፃሩ በጦር ሜዳ በማሰማራት የጥይት ሲሳይ እያደረጋቸው ስለሚገኝ የጋሞ ዞን ህጻናት ፓርላማ ኢሰብአዊ ድርጊቱን በእጅጉ ያወግዛል "ብላለች።
ህጻን ሜሮን አክላም "ይህንን ጭካኔ የተሞላበት የህወሓት ድርጊት የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መብት ኮንቬንሽንና የአፍሪካ ህፃናት መብት ደህንነት ቻርተር ተቀብለው የፈረሙ ሀገራት በአፋጣኝ ሊያስቆሙ ይገባል" ስትል ጠይቃለች።
"በትግራይ ክልል የሚገኙ ህፃናት ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ሰቆቃ የዓለም ማህበረሰብ እንዲሁም ሰው የሆነ ሁሉ በአንድ ድምጽ ሊቃወም ይገባል " ያለው ደግሞ የፓርላማው አባል ህፃን ሰርካለም ካሣሁን ነው።
"ህፃናት ትምህርት እንጂ ጦርነት አያስፈልጋቸውም ያለው" ህፃን ሰርካለም ይህን አረመኔያዊ ተግባር እየተመለከቱ ዝመታ የመረጡ የዓለም መንግስታት የጉዳዩ ተባባሪ ይሆኑ ይሆን የሚል ጥራጥሬ አሳድሮብኛል" ሲል የህወሓት አረመኔያዊ ድርጊት ያሳደረበትን ጭንቀት ገልጻል።
ትውልድ የማጥፋት ዘመቻ እየፈጸመ ያለው አሸባሪ ቡድን ለህግ እንዲቀርብ የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መብት ኮንቬንሽና የአፍሪካ ህፃናት መብት ደህንነት ቻርተር አባል ሀገራት መስራት እንደሚገባቸው ጠቁሟል።
በጋሞ ዞን ሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ የህፃናት መብት ደህንነት ማስጠበቅ ባለሙያ ወጣት ሳሙኤል ከኒቶ በበኩሉ "ህፃናት በለጋ ዕድሜያቸው ትምህርትና የወላጆች እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል" ብሏል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መብት ኮንቬንሽንና የአፍሪካ ህፃናት መብት ደህንነት ቻርተር ስምምነቶችን ተቀብላ የፈረመች ሀገር መሆኗን አስረድቷል።
በሁለቱም ስምምነቶች ህፃናት በውትድርና መሳተፍ እንደሌለባቸውና ድርጊቱ ሲፈጸምም አባል ሀገራት ማውገዝ እንዳለባቸው በግልፅ መደንገጉን አመላክተዋል።
"የወላጆች እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ህፃናት ጦር መሣሪያ በጫንቃቸው ተሸክመው ባልበሰለ አዕምሯቸው ወደ ጦር ግንባር መሰማራታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረውን የአገራትን ስምምነት በጉልህ የጣሰ ተግባር ነው" ሲል ኮንኗል።
"መንግስት ህፃናት ለሰብአዊ ቀውስ እንዳይዳረጉ ፣ የትግራይ አርሶ አደርም ግብርናውን በአግባቡ እንዲያከናውንና የጥሞና ጊዜ እንዲያገኝ የተናጥል ተኩስ አቁም ያደረገ ቢሆንም ውሳኔውን አሻፈረኝ ያለው አሸባሪው የህወሓት ቡድን ዳግም የትግራይ ህዝብና ህፃናትን ለመከራ መዳረጉ ይብቃህ ሊባል ይገባል" ሲል ወጣት ሳሙኤል ጠይቋል።