ቀጥታ፡

በዋሽንግተን ዲሲና በሙኒክ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለአገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 22-2013 (ኢዜአ) በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲና በጀርመን ሙኒክ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍና ለተለያዩ የልማት ስራዎች የሚውል 100 ሺህ ዶላርና 15 ሺህ ዩሮ ማዋጣታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲና በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዙሪያ የተከናወኑ ስራዎችን አብራርተዋል።

በዚህም በሳምንቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሠላምና የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሓፊ የፖለቲካና የሠላም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሮዝመር ዲካርሎ በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
በቆይታቸውም ጸሓፊዋ በሰሜን ኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም እየተገበረ መሆኑንና አሸባሪው ቡድን በተቃራኒው እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ ገለፃ ተደርጎላቸዋል ብለዋል።

በመሆኑም የመንግስታቱ ድርጅት በዚህ ጉዳይ ድምጹን ማሰማት እንዳለበት ማብራሪያ ተሰጥቷል ነው ያሉት።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም የልማት ጉዳይ በመሆኑ ዓለምዓቀፍ መልክ መያዝ እንደሌለበት እንዲሁም ሱዳን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በሚፃረር መልኩ የምትፈጽመው ተግባር ተገቢ እንዳልሆነ እንዲያውቁት ተደርጓል ብለዋል አምባሳደር ዲና።

በተጨማሪም በሳምንቱ መገባደጃ ላይ የአልጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራማታን ላማምራ በኢትዮጵያ ባደረጉት የስራ ጉብኝት ወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ገለጻ እንደተደረገላቸው ተናግረዋል።

አልጄሪያ የዓረብ ሊግ አባል እንደመሆኗ የሊጉ አድልዎ የተሞላበት አካሄድ ልክ አለመሆኑም ለሚኒስትሩ ማብራሪያ ተሰጥቷል ብለዋል።

ከዚህ ጎንለጎን በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በብዙ መልኩ ከአገራቸው ጎን መሆናቸውን ያሳዩበት ነበር ብለዋል።

በጃፓን፣ በኬንያ፣ በአሜሪካ፣ በአውስትራሊያና በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች በተለያየ መልኩ ስለ አገራቸው ወቅታዊ ሁኔታ እንዲያውቁ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በዚሁ መሰረት በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የሚውል 100 ሺህ የአሜሪካን ዶላር አዋጥተዋል ብለዋል።

በተመሳሳይ በጀርመን ሙኒክ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተለያዩ የልማት ስራዎችን ማገዝ የሚያስችል 15 ሺህ ዩሮ ማዋጣታቸውን አክለዋል።

ለቃል አቀባዩ በዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር እንቅስቃሴ፣ የጅቡቲ ድንበር አካባቢ ጉዳይ፣ የሱዳን ወቅታዊ ሁኔታና በአልሸባብ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎች ከጋዜጠኞች ቀርበውላቸዋል።

አምባሳደር ዲና በምላሹ አንዳንድ ጉዳዮች ጊዜያቸውን ጠብቀው መልስ የሚያገኙ ናቸው ብለዋል።

የአልሸባብን እንቅስቃሴ በተመለከተ ቡድኑ አልፎ አልፎ የሚያደርገው እንቅስቃሴ እንደወትሮው ሁሉ የሚገታ ይሆናል ብለዋል።

ሱዳን አሁንም የተለመደ ተግባሯን በመቀጠሏ ኢትዮጵያ "ይህ ነገር አያስኬዳችሁም እረፉ እያለች ትገኛለች" ብለዋል አምባሳደር ዲና።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም