ለሰራዊቱ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በገንዘብና በዓይነት ተሰብስቧል..የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
ለሰራዊቱ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በገንዘብና በዓይነት ተሰብስቧል..የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር
ሐዋሳ ሐምሌ 22/2013 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት የተቃጣውን ጦርነት ለመመከት በግዳጅ ላይ ለሚገኘው ሰራዊት ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በገንዘብና በዓይነት መሰብሰቡን የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
የሐዋሳ ከተማ ወጣቶች “ደሜን ለኢትዮጵያዬ” በሚል መርህ ለመከላከያ ሠራዊት የደም ልገሳ መርሃ ግብር ዛሬ ጀምረዋል።
ወጣቶቹ የሃገርን ህልውና ለመፈታተን የተነሳውን አሸባሪውን ህወሓት ለመደምሰስ ከመከላከያ ጎን በመሰለፍ እስከ ህይውት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የደም ልገሳ መርሃ ግበሩን ያስጀመሩት የአስተዳደሩ ምክትል ካንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ እንዳሉት የከተማው ነዋሪዎችና አመራሮች ሀገር ለማፍረስ የሚፍጨረጨረውን የጁንታ እንቅስቃሴ ለመቀልበስ ከተሰለፈው ሰራዊት ጎን በመቆም አጋርነታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ።
በተለይ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች የወር ደመወዛቸውን ከመለገስ ባለፈ ህብረተሰቡን በማስተባበር ሀብት ለማሰባሰብ በየደረጃው ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ዛሬ የተጀመረው የደም ልገሳ መርሀ ግብርም የጥረቱ አንድ አካል መሆኑን አመልክተዋል ።
ለሰራዊቱ እስካሁን ሀብት በማሰባሰብ ረገድ ከከተማው አስተዳደርና ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች በጥሬ ገንዘብ 30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
በአይነት ደግሞ 100 ኩንታል በሶና 150 የቀንድ እንስሳት ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።
የተሰበሰበውን ድጋፍ በቅርቡ ለመከላከያ ሰራዊት ለማስረከብ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
ሰራዊቱን በሰው ኃይል ለማጠናከር 1 ሺህ 300 ወጣቶች በራሳቸው ፈቃድ ተመዝግበው ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የህወሐት ቡድን በስልጣን በነበረበት ጊዜ በዘረጋቸው መረቦች የህዝቡን ስነ ልቦና ለመረበሽ የለመደበትን ወሬ አሁንም እየነዛ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከወትሮ በተለየ መንገድ የከተማውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ማህበረሰቡን ያሳተፈ የጸጥታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ከንቲባው አስታውቀዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የከተማው አስተዳደር ወጣቶች ሊግ የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ ወጣት ስንታየሁ ግርማ በበኩሉ "ሃገርን ከጥፋት ለመታደግ በግዳጅ ቀጠና ለሚገኘው ሰራዊታችን ደጀን መሆናችንን ለመግለጽ የከተማውን ወጣቶች ያሳተፈ የደም ልገሳ መርሀ ግብር ተዘጋጅቷል" ብሏል።
በዛሬው ዕለት በደም ልገሳ ከሚሳተፉ ወጣቶች 2 ሺህ 500 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱን አመላክቷል።
ወጣቱ በደም ልገሳና በሌሎች ለሰራዊቱ እያደረገ ካለው ደጀንነት በተጨማሪ በዘመቻው ለመቀላቀል ዝግጅት በማጠናቀቅ ጥሪ እየተጠባበቀ መሆኑን ተናግሯል።
ወጣቱ ከጸጥታ አካላት ጎን በመሆን በየአካባቢው የህዝብ አንድነትና ሰላም የሚያውኩ ሰርጎ ገቦችን በማጋለጥ ጸጥታ የማስጠበቅ ስራ ላይ መሰማራቱን አስታውቋል።
በደም ልገሳ ከተሳተፉ መካከል በሐዋሳ ከተማ የታቦር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ታዛቢ ታሪኩ ሃገሩን ከጠላት ለመታደግ እየተዋደቀ ላለው የመከላከያ ሠራዊት አጋርነቷን ለማረጋገጥ ደም መለገሷን ተናግራለች።
"አንድ ላይ በመዝመት ሀገርን ለመፈታተን የታወጀውን ጦርነት እንመክታለን" ያለችው ወጣቷ ህወሓት ህጻናትን በመመልመል ለጦርነት እየማገደ ያለውን ተግባር የዓለም ማህበረሰብና የትግራይ ነዋሪዎች እንዲያወግዙ ጠይቃለች።
ለሀገር ሉዓላዊነትና ለህዝቦች ሠላም ውድ ህይወቱን እየገበረ ላለው ለመከላከያ ሠራዊት ደጀንነቱን ለማሳየት ደም መለገሱን የተናገረው ደግሞ የታቦር ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሳሙኤል ቱጃ ነው።
ለሰራዊቱ ያለውን ደጀንነት በደም ልገሳ ሳይወሰን እስከ ግንባር በመዝመት እንደሚያረጋግጥ ገልጻል።