ቀጥታ፡

ከሳዑዲ ዓረቢያ ከተመለሱ 41 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን አብዛኞቹ ወደ አካባቢያቸው ተመልሰዋል - የሠላም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣  ሃምሌ 22/2013(ኢዜአ) ከሳዑዲ ዓረቢያ ከተመለሱ 41 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን መካከል አብዛኞቹ ወደ የአካባቢያቸው መመለሳቸውንና 60 ሺህ ገደማ የሚሆኑት አሁንም በሳዑዲ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የሠላም ሚኒስቴር ገለጸ።

በሠላም ሚኒስቴር የሕግ ማስከበር ዳይሬክተር አቶ አምባዬ ወልዴ ተመላሾቹ ስለሚገኙበት ሁኔታ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተገኝተው መግለጫ ሰጥተዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በሁለት ሳምንት ውስጥ 41 ሺህ 873 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

ተመላሾቹ ኢትዮጵያዊያን ከትግራይ፣ ከአማራ፣ ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልሎች የሄዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ወደ አካባቢያቸው ቢመለሱም በዘላቂነት መቋቋም እንዲችሉ ከፌዴራል ሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽንና ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ይሰራል ብለዋል።

በሌላ በኩል አሁንም በሳዑዲ ዓረቢያ 60 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ሁኔታው በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዜጎችን መመለስ ብቻ መፍትሄ አለመሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በ2006 ዓ.ም ብቻ ከ150 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ አገራቸው እንደሚለሱ መደረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም