ቀጥታ፡

ወጣቱ የሠራዊቱን የአገር ሕልውና የማስጠበቅ ተግባር ውጤታማ ለማድረግ ድጋፍ እያደረገ ነው

አዲስ አበባ ሀምሌ 22/2013 (ኢዜአ) የመከላከያ ሠራዊት የአገር ሕልውና ለማስጠበቅ እያደረገ ባለው ዘመቻ ወጣቱ ከጎኑ በመቆም በተለያየ መልኩ ድጋፍ እያደረገ ነው።
የአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ወጣቶች ሊግ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ለሠራዊቱ አጋርነታቸውን ለማሳየት ደም ለግሰዋል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አማካሪ አቶ ተመስገን ኃይለማርያም ለኢዜአ እንዳሉት፤ ወጣቱ የመከላከያ ሠራዊቱ እየከፈለ ያለው መስዋዕትነት ለውጤት እንዲበቃ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።

የአገር መከላከያ ሠራዊቱን ከመቀላቀል ባሻገር በቁሳቁስ፣ በገንዘብና በሃብት ማሰባሰብ ሂደት ጉልህ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።    

በክፍለ ከተማ ደረጃ ከ300 በላይ በጎችና 18 ሰንጋዎችን ጨምሮ 18 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ሃብት በማሰባሰብ ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ መደረጉንና በዚህ እንቅስቃሴ የወጣቶች ድርሻ ከፍያለ እንደሆነም ተናግረዋል።   

"እኛ እያለን ኢትዮጵያ አትፈርስም!" በሚል የክፍለ ከተማው ወጣቶች ወደ ግንባር በመሄድ ሠራዊቱን እየተቀላቀሉ እንደሆነም አክለዋል።  

የክፍለ ከተማው ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ሰብሳቢ ተካ ደመቀ በበኩሉ፤ የደም ልገሳው ወጣቶች ቀዳሚና ለሌሎች ዓርአያ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጿል።

ለመከላከያ ሠራዊቱ ድጋፍ ለማድረግ በሊግ ደረጃ ከባለሃብቶችና ከወጣቶች ሃብት እየተሰባሰበ መሆኑንም አክሏል።  

ከደም ለጋሾቹ መካከል ወጣት ኃይማኖት ዘመኑ 'ዛሬ ለመከላከያ ሠራዊት ደሜን ለግሻለሁ፤ ከዚህ ባለፈም ወደ ግንባር በመሄድ የህልውና ዘመቻውን ለመቀላቀል ዝግጁ ነኝ ሲል ተደምጧል።  

የመንግሥት ሠራተኛ መሆኑን የገለጸው ወጣት ኃይማኖት "የአንድ ወር ደመወዜን ለመከላከያ ድጋፍ እንዲውል ለመስጠት ቃል እገባለሁ" ብሏል።  

ወጣቱ አገር የምትቀጥለው በመስዋዕትነት መሆኑን በመረዳት ራሱን ማዘጋጀት አለበት ነው ያለው።

ወጣት ናትናኤል አበራ በበኩሉ፤ የመከላከያ ሠራዊቱ የአገር ህልውናን የማስቀጠል ተልዕኮ እንዲሳካ እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድነት መደገፍ አለብን ብሏል።

"የዛሬ ደም ልገሳ ሠራዊቱ ለከፈለው መስዋዕትነት የማመስገኛ ሁነት ነው" ሲል ተናግሯል።

በተያያዘ ዜና በአዲስ አበባ የንፋስ ሥልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፋቸውን ለመግለጽ ደም ለግሰዋል፡፡

በደም ልገሳው የተሳተፉት ነዋሪዎች ለመከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ወገንተኝነት ለማሳየት ደም በመለገስ መጀመራቸውን ነው የተናገሩት፡፡

'በሠላም ወጥተን እንድንገባ ህይወቱን ለሰጠን መከላከያ ሠራዊታችን ደም በመስጠት ብቻ አናቆምም' ያለችው ወጣት ማህደር መስፍን እንደ አስፈላጊነቱ ለመዝመት ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።

ወጣት ቅድስት ዘገየ በበኩሏ ሁላችንም ግንባር መሄድ ባንችል እንኳን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ሠራዊቱን ከመደገፍ ወደኋላ አንልም ብላለች።

የደም ልገሳው አስተባባሪ ወጣት አብዱልሀኪም ቡልጉ፤ በዛሬው መርሃ ግብር ብቻ ከአንድ ሺህ በላይ የክፍለ ከተማው ወጣቶችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ገልጿል።

ደም ከመለገስ ባሻገር የሽብርተኛውን የህወሓት ቡድን ሴራ ለማክሸፍ 500 የክፍለ ከተማው ወጣቶች ሠራዊቱን ለመቀላቀል  ወደ ግንባር መሸኘታቸውንም ተናግሯል።     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም