ቀጥታ፡

ከአማራ ክልል ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ258 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

ባህርዳር፤ ሐምሌ 22/2013(ኢዜአ) ከአማራ ክልል በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩ የተለያዩ የግብርና ምርቶች 258 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በበጀት ዓመቱ  ወደ ውጭ  ከተላኩት የግብርና ምርቶች  ውስጥ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ሰሊጥ ፣ አኩሪ አተር፣ ቦሎቄ፣ ማሾ፣ ቡናና ዓሣ እንደሚገኙበት በቢሮው የእንስሳት ተዋፅኦ ግብይት ተተኪ ዳይሬክተር አቶ የኔገዳም ተስፋ ለኢዜአ ገልጸዋል።

572 የዳልጋ ከብቶች፣ 19 ሺህ 643 በግና ፍየሎች ሌላው ገቢ ያስገኙ የግብርና ዘርፎች መሆናቸውን አመላክተዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ ምርቶቹ የተላኩት ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ሕንድ፣  መካከለኛው ምሥራቅና   አፍሪካ ሀገራት ሲሆን ፤ ገቢው ከዕቅዱ ጋር ሲነጻጸር  አፈጻጸሙ 72 በመቶ ነው።

በቀጣይ በክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ምርቶቹን በብዛትና  ጥራት  ወደገበያ ማቅረብ፣ ህገወጥ ንግድና ደላሎችን በመቆጣጠር የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አመልክተዋል።

በክልሉ የአድማስ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ መሰረት ወርቄ   ፤ ዩኒየናቸው የግብርና  ምርቶችን   ወደ ውጭ  በመላክ ገቢውን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 16 ሺህ ኩንታል አኩሪ አተር ወደ ቻይና፣ ሲንጋፖርና  ሕንድ በመላክ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ 10 ሺህ 670 ኩንታል ቦሎቄ ወደ አውሮፓ በመላክ  ከ963 ሺህ ዶላር  በላይ ገቢ  ማግኘታቸውን ያስታወቁት ደግሞ  የራስ ጋይንት ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ  አቶ መልካሙ ፋንታሁን ናቸው።

በተያዘው የበጀት ዓመት ተጨማሪ 10 ሺህ ኩንታል ቦሎቄ ለመላክ ማቀዳቸውንም ጠቁመዋል።

በአማራ ክልል በ2012 የበጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ289 ሚሊዮን 900 ሺህ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱ ከንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም