ቀጥታ፡

ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፈው አሸባሪውን ቡድን ለመፋለም ዝግጁ መሆናቸውን በወልዲያ ከተማ ወጣቶች ገለጹ

ወልዲያ ፤ ሐምሌ 22/2013(ኢዜአ)  ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፈው አሸባሪውን የህወሃት ቡድን ለመፋለም ዝግጁ መሆናቸውን በወልዲያ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ገለጹ።

ከወጣቶቹ መካከል የአራተኛ ዓመት የህግ ተማሪ የሆነው አሰፋ ቦጋለ እንዳለው፤ ለሃገር ክብር ደንታ የሌለው የህወሓት ቡድን የደቀነው ጦርነት የኢትዮጵያን ህልውና እየተፈታተነ ነው።

አሸባሪ ቡድኑ የአማራን ህዝብ ለማዳከምና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውጭና ከውስጥ ጠላቶች ጋር ተባብሮ እየሰራ መሆኑንም አመልክቷል።

ዘራፊና አሸባሪ ቡድኑ የከፈተውን ጦርነት መመከትና ቡድኑን እስከ መጨረሻው መፋለም ጊዜ የማይሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ተናግሯል።

 ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ የጥፋት ቡድኑን ለመፋለም  ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

የክልሉን መንግስት የክተት ጥሪ መቀበሉን የተናገረው ወጣቱ፣ ኢትዮጵያ አሁን ያጋጠማት ችግር እስኪወገድ ድረስ የድርሻውን እንደሚወጣም አስታውቋል።

መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በተነሳሽነት የመጡ ወጣቶችን በማሰልጠንና በማስታጠቅ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥም ጠይቋል።

በወልዲያ ከተማ የጣይቱ ብጡል  ትምህርት ቤት መምህር አማኑኤል አማረ በበኩሉ  "የህወሓት ከሃዲ ቡድን እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ ሃገር መሆን አትችልም በሚል ሴራ እንድትፈርስ እየሰራ ነው" ብሏል።

ሃገርን ለጠላት አጋልጦ ለመስጠት ሲተጋ የኖረው ቡድን አሁን በለየለት መንገድ የኢትዮጵያ ጠላት ሆኖ እየወጋት መሆኑን ተናግሯል።

ከሁለት ሳምንት በፊት የቴክኒክና የአካል ብቃት ስልጠና መውሰዱን ጠቅሶ፤ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን የሽብር ቡድኑን የጥፋት ተግባር ለማክሸፍ መዘጋጀቱን ገልጿል።

የሀገር ህልውና ለመጠበቅ ሁሉም ዜጋ ሃላፊነት እንዳለበትም አመልክቷል።

መንግስት ተነሳሰተው ያሉትን ወጣቶች በማደረጀት አሰልጥኖና አስታጥቆ ወደ ግንባር በማሰማራት ሃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቋል።

የህወሓት አሸባሪ ቡድን በአካባቢው የፈጠረው ውዥንብር ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን የተናገረው ደግሞ  በከተማው በባጃጅ ታክሲ አሽከርካሪነት የተሰማራው  ወጣት ሳሚ ዓለሙ ነው።

ቡድኑ የፈጠረውን ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራ ለማክሸፍ በግንባር ቀደምነት ለመቆም መዘጋጀቱን ገልጿል።

ህብረተሰቡም በጁንታው በበሬ ወለደ ወሬ  ውዥንብር ሳይደናገር የአሻባሪውን ሴራ ለማክሸፍ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተናግሯል።

በአካባቢው ወጣቱ የጁንታውን ሃይል ለመፋለም ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ጠቅሶ፤መንግስት የአጭር ጊዜ ስልጠና በመስጠት  አስታጥቆ ማሰማራት እንዳለበት ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም