ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ለመበተን የተነሳውን አሸባሪ ቡድን ለመፋለም ተዘጋጅተናል --- የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች

ባህር ዳር ሐምሌ 21/2013 (ኢዜአ) ሀገር ለመበተን የተነሳው አሸባሪው የህወሓት ቡድንን በመፋለም እየፈፀመ ያለውን ወረራ ለመቀልበስ መዘጋጀታቸውን ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በተካሄደ ው ሰልፍ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ገለጹ።

ከወጣቶቹ መካከል  ገነት መሴ ከሀዲና አሸባሪው ቡድን  ኢትዮጵያን ሊያፈርሳት  አይችልም፤ ወደሰልፉ የመጣሁትም  ቡድኑን በማውገዝ ከመከላከያና ከመላ ሀገሪቱ ለተውጣጡ ልዩ ኃይሎች ጎን  ለመግለፅ ነው ብላለች። 

ወደ ግንባር ለመዝመትም ተመዝግባ እየተጠባበቀች መሆኗን የተናገረችው ወጣቷ ፤ ኢትዮጵያን ከአሸባሪውና ቡድን ለማላቀቅ በምናደርገው ዘመቻም ድል እናደርጋለን ስትል ገልጻለች።

ወጣቱም በህወሃት ርዝራዥ  በሚነዛው የሽብር ወሬ ሳይረበሽ አንድ ሆኖ በመቆም የሀገሩን ሉአላዊነት ሊያስጠብቅ እንደሚገባ አሳስባለች።

በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱን ከብተና ለመታደግም ወጣቱ ከመከላከያና ከልዩ ሃይሉ ጎን በመቆም አካባቢውን ነቅቶን ሊጠብቅ እንደሚገባም አመለክታለች።

ለህዝባች፣ ለልጆቻችን፣ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ሲባል ተደራጅተን  አካባቢውን ነቅተን በመጠበቅ አሸባሪውንና ከሀዲውን ቡድን ማስወገድ ይኖርብናል ብላለች።

ወጣት ዘመኑ ቢያዝን በበኩሉ፤ አሸባሪው ቡድኑ አማራን ገዢና በዝባዥ  አድርጎ  በተሳሳተና  በተዛባ የሀሰት ትርክት እንዲታይ  በማድረጉ ከሌሎች  ብሔረሰቦች  ጋር  ሲያጋጨውም መኖሩን አውስቷል።

በዚህም ከክልሉ ውጭ በሚኖረው የአማራ ህዝብ ላይ ከቄየው የመፈናቀል፣  የመሰደድ ፣ የመገደልና ሌሎች ግፎች እንዲፈጸሙበት በማድረግ ታሪክ የማይረሳው ሥራ መፈጸሙን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም "በአማራ ላይ የማወራርደው ሒሳብ አለኝ"  በሚል የአማራን  ህዝብ  አንገት  ለማስደፋትና ኢትዮጵያን ለመበተን  እኩይ ተግባሩን በተግባር አሳይቷል ብሏል።

"እኛ የአማራ ወጣቶች በአማራዊና ኢትዮጵያዊ ጀግንነት ወደ ግንባር በመዝመት  አሸባሪ ቡድኑን ለመደምሰስ ቁርጠኛ ነን" ሲል አስታውቋል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የቻለ ወደ ግንባር በመዝመት ያልቻለ ደግሞ በገንዘቡና በእውቀቱ ስንቅና ትጥቅ በማቅረብ የጀመረውን አኩሪ ተግባር እንዲያጠናክርም ጠይቋል።

ወጣት ዘመኑ እንዳለው፤ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራትና ድርጅቶች አሸባሪው ህወሓትን በመደገፍ  በኢትዮጵያ ላይ ጫና እየፈጠሩ በመሆኑ ህዝቡ ከመንግስት  ጎን በመሰለፍ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በጋራ መመከት ይኖርበታል።

በባህር ዳር ከተማ ዛሬ በተካሄደ ሰልፍ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አባት አርበኞች  ፣የመንግስት  ሠራተኞች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ቀደም  ብሎ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም