ወጣቱ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በመደምሰስ የአባቶቹን ገድል መድገም አለበት--- አባት አርበኞች - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በመደምሰስ የአባቶቹን ገድል መድገም አለበት--- አባት አርበኞች
ባህር ዳር፤ ሐምሌ 21/2013(ኢዜአ) ወጣቱ ኢትዮጵያን የመታደግ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በመደምሰስ የአባቶቹን ገድል መድገም እንዳለበት የአማራ ክልል አባት አርበኞች ማህበር አባላት አሳሰቡ።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክተት ጥሪን በመደገፍ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው ሰልፍ የተካፈሉ ማህበር አባላት በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት የተዳፈረውን ወንበዴ ቡድን ለመደምሰስ እየተደረገ ያለው ጥረት መጎልበት አለበት።
በሀገር ህልውና ላይ የዘመተውን ቡድን ግብዓተ መሬት ለማስገባትም ጥሪ ከቀረበላቸው በግንባር ለመሰለፍ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
ከማህበሩ አባል አባት አርበኞች መካከል የ10 አለቃ ያየህይራድ ታዬ ፤ የህወሓት አሸባሪ ቡድን በሥልጣን ዘመኑ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያን ላይ መጠነ ጉዳት ሲያደርስ እንደነበር አውስተዋል።
የቡድኑን እኩይ ሴራ የተረዳው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተጀመረውን መጠነ ሰፊ ሀገርን የመታደግ ዘመቻ በማጠናከር የጀንታውን ዕድሜ ማሳጠር ይገባዋል ብለዋል።
ወደ ግንባር ለመሄድ እየተጠባበቁ መሆናቸውን የተናገሩት የ10 አለቃ ያየህይራድ፤''ቡድኑን ለማጥፋት ከመስራት የበለጠ ጉዳይ የለኝም'' ሲሉም ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።
ሌላው አባት አርበኛ የመቶ አለቃ በላቸው ፈንቴ ፤ ህወሓት ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ኢትዮጵያን በዘር ለመከፋፈል አልሞ የተነሳ አጥፊ ቡድን መሆኑን አስረድተዋል።
ቡድኑ የትግራይ ተወላጆች ጭምር ለእልቂት እየዳረገ በመሆኑ በኢትዮጵያ ሕዝብ የተባበረ ክንድ ሊደቆስ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ወጣቱ የጀመረውን ኢትዮጵያን የመታደግ እንቅስቃሴ አጠናክሮ አሸባሪውን የህወሓት ቡድንን በመደምሰስ ላይ የአባቶቹን የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ገድል መድገም አለበት ብለዋል።
"ዕድሜዬ ለጦርነት የማይፈቅድ ቢሆንም ኢትዮጵያ ስትፈርስ ቁጭ ብዬ አላይም" ያሉት የመቶ አለቃ በላቸው፣ አሸባሪውን ቡድን ግንባር ሂዶ ለመዋጋት እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።
የአማራ ክልላዊ መንግሥት የክተት ጥሪ ተገቢና ወቅታዊ ነው ያሉት ደግሞ አባት አርበኛ ገረመው ይግዛው ናቸው።
አሸባሪው ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች ላይ ጦርነት ይክፈት እንጂ፤ የመጨረሻ ዓላማው ኢትዮጵያን ማፈራረስ እንደሆነም አመልክተዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያውያን እያደረጉት ያለውን ሀገርን የመታደግ የህልውና ትግል በማጠናከር ቡድኑን ከምድር ገጽ ላይ ማጥፋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
''የማይወዷትን ሀገር ሲመሩ የነበሩ ሌባ፣ ከሃዲና ባንዳዎች ናቸው፤ ዛሬም ከኢትዮጵያ የጥንት ጠላቶች ጋር በመወገን ኢትዮጵያን እየወጓት ይገኛሉ ብለዋል።
ይህንን የጥፋት ሴራ ለመከላከል በተለይ ወጣቱ የጀመረውን ኢትዮጵያን የማዳን ዘመቻ ማጠናከር እንዳለበትና እሳቸውም ግንባር ድረስ ሄደው ለመፋለም መወሰናቸውን አስታውቀዋል።