በክልሉ የተመዘገቡ ስኬቶችን የበለጠ በማጠናከር የያዝነው ግብ ለመድረስ መትጋት ይኖርብናል... አቶ ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተመዘገቡ ስኬቶችን የበለጠ በማጠናከር የያዝነው ግብ ለመድረስ መትጋት ይኖርብናል... አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዳማ ፤ ሐምሌ 21/2013 (ኢዜአ) በክልሉ የተመዘገቡ ስኬቶችን የበለጠ በማጠናከር ከያዝነው ግብ ለመድረስ ለአፍታም ሳንዘናጋ መትጋት ይኖርብናል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
በአዳማ ከተማ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የግምግማ መድረክ ዛሬ ሲጠናቀቅ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ በሰጡት የስራ መመሪያ አሁን በስመዘገብነው ስኬት መዘናጋት ሳይሆን ለቀጣይ ድላችን ተጨማሪ ስንቅና አቅም በማድረግ መረባረብ አለብን ብለዋል።
በተገኘው ጅምር ውጤቶች መኩራራት ለውድቀታችን በር የሚከፍቱ ከመሆናቸውም ባለፈ እንደ ክልልና ሀገር ለማሳካት ከያዝነው ግብ እንዳንደርስ የሚያደርግ በመሆኑ ለአፍታም ሳንዘናጋ መትጋት ይኖርብናል ሲሉ ገልጸዋል።
የተናበበና ወጥነት ያለው አመራር ለተሻለ የስራ አፈፃፀም ስኬት ወሳኝ በመሆኑ በዕቅድና አሰራር በመናበብ በአዲሱ የበጀት ዓመት በሁሉም መስኮች አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ መረባረብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የኦሮሞ ህዝብ አንድነቱን በማጠናከርና ልዩነትን በማጥበብ የውስጥ ጥንካሬ እንዲጎለብት አመራሩ መስራት አለበት ያሉት ደግሞ የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ናቸው።
አቶ ፍቃዱ፤ጠባቂነት አንዱ የጥገኝነት ምልክት ነው፤ የኦሮሞ ህዝብ አንድነት ለሀገራችን አሸናፊነት ወሳኝ ነው ብለዋል።
በየደረጃው ያሉ አመራሮች ዘንድ የሚስተዋሉ የአመለካከት ክፍተቶችና ያለመናበብ ችግር አሁንም የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል።
ዋና ዋና ግቦችን ለማሳካት እንቅፋቶች የሆኑ ችግሮችን መለየትና ቀጣይ የአቅጣጫ በማስቀመጥ ረገድ መድረኩ ወሳኙ ነበር ብለዋል።
በቤተሰብ ደረጃ ብልፅግናን ማረጋገጥ የሚቻለው የሚመዘገበው ለውጥና ዕድገት በእያንዳንዱ ነዋሪዎች ቤት መግባት ሲችል መሆኑን አስረድተዋል፣
ይህን ለማድረግ የክልሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ዕቅድ በቤተሰብ ደረጃ ተግባራዊ በማድረግ ነው ብለዋል።
በዚህም ከቀበሌ እስከ ክልል ያለው አመራር ህዝብን ባሳተፈ መልኩ በአካባቢው የሚያከናውነውን ዕቅድ በዝርዝር ሊፈፅመው የሚችል መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለህዝቡ ሁሉን አቀፍ ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ አቅም የመፍጠር ጭምር ሊሆን እንደሚገባም አመልክተዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ዞኖችና ተቋማት ዕውቅና መሰጠቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ከአዳማ ዘግቧል።