ቀጥታ፡

ድሬዳዋን አንዷ የቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን ማዕከል የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላሉ…ዶክተር አብርሃም በላይ

ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 21/2013(ኢዜአ)ድሬዳዋ ከተማን የኢትዮጵያ አንዷ የቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ።

ሚኒስትሩ ችግኝ በመትከል፣ የአቅመ ደካሞችን ቤቶች በማደስ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዘሬ በድሬዳዋ ከተማ አስጀምረዋል።

ዶክተር አብርሃም በመርሃ-ግብሩ ላይ እንዳሉት ድሬዳዋ ከተማን አንዷ የቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል።

“ድሬዳዋ ተገኝተን ችግኝ በመትከል፣የአቅመ ደካሞችን ቤቶች በማደስ የበጎ ተግባር ስራ ላይ በመሰማራታችን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና የሰራተኞች ተወካዮች እጅግ ተደስተናልም” ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በድሬዳዋ በዘጠኙ ቀበሌዎች በሙሉ የበጎ ፍቃድ ሥራን እንደሚያከናውንም ዶክተር አብርሃም ገልፀዋል።

በዚሁ ጊዜ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ቡህ የበጎ ፍቃድ የወጣቶች የልማት ተግባራት ለአገርና ለአስተዳደሩ ነዋሪ ኑሮ መሻሻል አበርክቶው የጎላ ይሆናል ብለዋል፡፡

አስተዳደሩ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመቀናጀት የጀመሩት የበጎ ፍቃድ የልማት ስራዎች ትርጉም ያላቸው ውጤቶች የሚገኙባቸው እንደሚሆኑም ገልፀዋል።

እንደ ምክትል ከንቲባ አህመድ ገለጻ አገርን ከድህነት ለማላቀቅና ወደ ብልጽግና ለማሻገር በዘመናዊ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ውጤቶች መጠቀምና በነዚህ ዘርፎችም አቅምን መገንባት መሠረታዊ ነው።

በመሆኑም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድሬዳዋን ወደ ከፍታና ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለማሻገር ለሚደረገው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ መሳካት እያደረገ የሚገኘውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የመስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የከተማ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት፣ የሰላም አምባሳደር አገር አቀፍ በጎ ፍቃድ ተሣታፊ ወጣቶች፣ የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም