"በሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ የሚያዝም ሆነ የሚለቀቅ ቦታ የለም" --የአማራ ክልል የመንግሥት - ኢዜአ አማርኛ
"በሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ የሚያዝም ሆነ የሚለቀቅ ቦታ የለም" --የአማራ ክልል የመንግሥት
ሀምሌ 21/2013 (ኢዜአ) በሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ የሚያዝም ሆነ የሚለቀቅ ቦታ እንደሌለ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ገለጸ ፡፡
ለእኛ ጦርነቱን ማሸነፍ ማለት አሸባሪውን ትህነግ ነቅሎ መጣል ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ በቆራጥነት ትግል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በጦርነት አንዳንድ ጊዜ ወደፊት ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ ኋላ ማለት ያለና የነበረ የጦርነት ህግ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ማሸነፍንም ሆነ መሸነፍን አያመላክትም፡፡
ምክንያቱም በጦርነት ውስጥ አንድን ቦታ መልቀቅም ሆነ መያዝ ራሱን የቻለ የውጊያ ታክቲ በመሆኑ ነው፡፡ የዚህ የህልውና ጦርነት ግብ አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ከስሩ ነቅሎ በመጣል ክልላችንን እና ኢትዮጵያን ከአሸባሪው ኃይል ሙሉ በሙሉ ነጻ ማውጣት እንጂ ቦታ በመያዝና መልቀቅ የሚወሰን አይደለም፡፡
በዚህ መንገድ ሲለካ በእስካሁኑ ሂደት አሸባሪውን ቡድን ደግፈው የዘመቱም ሆነ የሚተማመኑባቸው ሁሉ በከፍተኛ ደረጃ እየተመቱና ድል እየተደረጉ በመሆኑ ትህነግ ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት ነው፡፡
ነገር ግን በውሸት ፕሮፓጋንዳ ‹‹ደባርቅን ልይዝ ነው፤ ወልድያ ልገባ ነው›› እያሉ ሰርጎ ገቦችን በመጠቀም የማኅበረሰቡን ስነ ልቡና ለመጉዳት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የተበላበት እቁብ ነው፡፡
በግልጽ እንደሚታውቀው የአማራ ህዝብ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በድጋፍ ሰልፍ፤ ወደ አውደ ውጊያው በመግባትም፤ በገንዘብ እና በአይነትም ለጦሩ ድጋፍ በማድረግ እያሳየ ያለው እንቅስቃሴ ስነ ልቡናው ከፍ ያለ እና ወትሮም የነበረ የአባቶቹ ስለሆነ በትህነግና በትህነጋውያን የውሸት ፕሮፓጋንዳ አይሸበርም፡፡
በተደጋጋሚ እንደተገለፀው ወረራ የተፈጸመብን በወልቃይትና አካባቢው፣ በዋግኽምራና ራያ ግንባር ሲሆን በዛሬው ውሏችን ከትናንትና ማታ ምሽት 3፡00 ጀምሮ ሞቅና ቀዝቀዝ እያለ ውጊያው ቀጥሏል፡፡
ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ታጋዮች አሸባሪውን ትህነግ ከያለበት ለቅሞ በመምታት ከፍተኛ ድል እያገኙ ሲሆን አሁንም በከፍተኛ ዝግጅትና ውጊያ በማድረግ ላይ ናቸው ብሏል፡፡
ውድ የማኅበራዊ ሚዲያ ወታደሮች በትዊተር፣ በፌስቡክና በዩቱብ አሸባሪው ትህነግ እያሰራጨው የሚገኘውን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመቀልበስ ረገድ እየተደረገ ያለው ርብርብና ትግል ሌላኛው ድል እየተገኘበት ያለ ነው ተብሏል፡፡
ነገር ግን አልፎ አልፎ በግንዛቤ ጉድለት ወይም በባንዳነት ለጠላት መረጃ የሚሰጡ ስላሉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እናሳስባለን፡፡
መላው ህዝባችን በሀገር ውስጥም በውጭም ያላችሁ ልጆቻችሁን፣ ባሎቻችሁንና ሚስቶቻችሁን በቀጥታ ነፍጥ አንግበው ወደ ጦርነት እንዲሄዱ መርቃችሁ ከመሸኘት ባሻገር በገንዘብ፣ ስንቅ በማዘጋጀት፣ የሞራል ድጋፍ በመስጠት በአጠቃላይ ሀቀኛ ደጀን በመሆን እያደረጋችሁት ያለው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው ፡፡ ለዚህም ከልብ እናመሰግናለን ብሏል ፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ጦርነት በአሸባሪው ትህነግ አማራን የማጥፋት፤ ሀገርን የመበተን ዓላማ ተይዞለት ረዘም ወዳለ የትጥቅ ትግል በማስገባት ኢትዮጵያን ለማጎሳቆል የታሰበ ስለሆነ አሁን የጀመራችሁትን ደጀንነት በከፍተኛ መነሳሳትና ወኔ እስከ ፍጻሜ ድረስ ተግባራዊ እንድታደርጉ እንጠይቃለን ሲል መልእክት አስተላልፏል፡፡
በአጠቃላይ መላው የክልላችን ነዋሪዎች ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ በውጭ የምትኖሩ ተወላጆች እና መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በገባንበት ህልውናን የማስጠበቅ ዘመቻ በአሉባልታና በውሸት ፕሮፓጋንዳ ሳንደናገር ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድና ወጥ የሆነ አቋም ይዘን ወደ ጦር ሜዳ ልንተም ይገባናል፡፡
መንገዳችን አንድ እና አንድ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም እኛን ለማጥፋት የማይተኛውን አሸባሪ ነቅሎ ማስወገድ ብቻ ነው፡፡ የአማራ መሬት ለአሸባሪው ትህነግ እሾህ እንጂ መቼም ቢሆን ዳቦ አይሆንም! ።ምንጭ፤- የአማራ ክልል ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት