ቀጥታ፡

ኢሰዴፓ ብሔርና ሃይማኖትን መሰረት አድርገው የሚነሱ ግጭቶችን እንደሚያወግዝ ገለጸ

አዲስ አበባ ነሃሴ 2/2010 የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢሰዴፓ/ ብሔርና ሃይማኖትን መሰረት አድርገው የሚነሱ ግጭቶችን እንደሚያወግዝ ገለጸ። መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች በሚነሱ ግጭቶች የሰው ህይወትና ንብረት ሳይጠፋ ቀድሞ ማስቆም ይገባዋል ሲልም አሳስቧል። የፓርቲው ሊቀ-መንበር ሼህ ሰይድ ይመር አሊ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት መንግስት ባለው ኃላፊነት ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት አስቀድሞ እርምጃ መውሰድ ይገባዋል። "በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው ሁከትና ብጥብጥ በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚደረግና የፖለቲካ ቁማር የሚጫወቱ አካላት የሚያስነሱት በመሆኑ ፓርቲው ይህን ተግባር ይቃወማል" ብለዋል። ምንም እንኳን የክልል መንግስታት ካልፈቀዱ የፌዴራል መንግስት ገብቶ አካባቢዎችን ማረጋጋት እንደማይችል ሕገ-መንግስቱ ቢያስቀምጥም የዜጎች ህይወትና ንብረት ሳይወድም መፍትሔ ሊሰጥ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገሪቱ እየታየ ያለውን ለውጥ ፓርቲዊ እንደሚደግፍና ሕብረተሰቡም ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የፓርቲው ልዩ ፀሐፊ አቶ ሶፍያን ዳውድ በበኩላቸው በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የመደመር ጽንሰ ሐሳብ እንደሚደግፉና በጅግጅጋ የተፈጸመውን ድርጊት እንደሚያወግዙ ተናግረዋል። ፓርቲው በሶማሌ ክልል በቤተ-ክርስቲያንና በዜጎች ላይ በተፈፀመው የግድያና ንብረት የማጥፋት ወንጀል የተሳተፉ አካላት ለሕግ ሊቀርቡ እንደሚገባ ገልጾ ለተጎጂ ቤተሰቦች ሐዘኑን ገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም