ቀጥታ፡

አሁን ያለንበት ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነት እና አብሮነትን ይጠይቃል--ሌተናል ጄነራል አሥራት ዴኔሮ

ሃምሌ 21/2013(ኢዜአ)"አሁን ያለንበት ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነት እና አብሮነትን የሚጠይቅ ነው" ሲሉ የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት የተቀናጀ ግብረ ኃይል ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አሥራት ዴኔሮ ገለጹ።

የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት የተቀናጀ ግብረ ኃይል ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አሥራት ዴኔሮ በዳንጉር ወረዳ ማንቡክ ከተማ በተፈናቃዮች ካምፕ በመገኘት ከህብረተሰቡ ጋር ተወያይተዋል።

ሌተናል ጄኔራል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሓት ህብረተሰቡ አንድ እንዳይሆን በርካታ የሀሰት መረጃዎችን እየፈጠረ ሲያሰራጭ ቆይቷል።

በተለያዩ የግል መገናኛ ብዙኃን ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የሚሰራጩ መረጃዎችም ህብረተሰቡን ለከፋ ችግር ዳርገውት መቆየታቸውን አብራርተዋል።

አሁንም ቢሆን አዕምሯቸው በጎ ነገር ማሰብ ስለማይችል ሌላ ችግር እንዳይፈጠር የአካባቢው ማህበረሰብ አንድነቱን ሊያጠናክር እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት የእርሻው ጊዜ እንዳያልፍ ከወረዳዎች ጋር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ በተለያየ ሁኔታ ፀጉረ ልውጦችን በሚያይበት ወቅት በአካባቢው ለሚገኙ የጸጥታ አካላት በማሳወቅ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በአካባቢው በተፈጠረው ሰላም ተረጋግተው መደበኛ ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።

የመከላከያ ሠራዊት ወደ መጠለያ ጣቢያ ከመጡ ጀምሮ እያደረገላቸው ስላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በጣቢያው ተጠልለው የሚገኙ ነዋሪዎችም የሚቀርቡ ድጋፎችን በተገቢው መንገድ ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም