በሲዳማ ክልል ሠራዊቱን ከደጀንነት በተጨማሪ በሰው ሃይል ለማጠናከር ድጋፉ እንደቀጠለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል ሠራዊቱን ከደጀንነት በተጨማሪ በሰው ሃይል ለማጠናከር ድጋፉ እንደቀጠለ ነው
ሀዋሳ፤ ሐምሌ 21/2013 ኢዜአ) በሲዳማ ክልል የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ከደጀንነት በተጨማሪ በሰው ሃይል ለማጠናከር የሚደረገው ድጋፍ እንደቀጠለ መሆኑ ተገለጸ።
በክልሉ ከ7 ሺህ በላይ ወጣቶች ተመዝግበው ለማሰማራት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ተመልክቷል።
የብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት አመራሮችና አባላት " ደማችን ለሠራዊታችን" መሪ ሃሳብ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደም በለገሱበት ወቅት የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ እንዳሉት ፤ የህወሓት ጁንታ በሃገሪቱ ላይ ያወጀውን ጦርነት ለመመከት ሁሉም የክልሉ ነዋሪ በቁጭት በመነሳት ደጀንነቱን እየገለጸ ነው።
በተለይ የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፀጥታው አካል በመንግስት የተሰጠውን ተልዕኮ በስኬት እንዲወጣ ሀብት ከማሰባሰብ በተጓዳኝ በሰው ሃይል ለማጠናከር እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ሠራዊቱን በሰው ሃይል ለማጠናከር በሁለት ዙር ልዩ ሃይል መዝመቱን ጠቅሰው፤ትግሉን ለመቀላቀል ፍላጎት ያላቸው ከ7 ሺህ በላይ ወጣቶች ተመዝግበው ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮ ለማሰማራት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀብት በማሰባሰብ ሂደቱም በአጭር ጊዜ ውስጥ 50 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ፣ በዓይነት ደግሞ 230 ሰንጋዎች፣ 600 በግና የፍየሎች፣እንዲሁም ስንቅ ከሁሉም አካባቢዎች ድጋፍ መደረጉን አመላክተዋል ።
ለመከላከያ ሠራዊት ደም ከለገሱት ውስጥ የጽህፈት ቤቱ የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ሃላፊ አቶ አስፋው ጎነሶ በበኩላቸው፤ አሸባሪው የህወሓት ጁንታ የሀገርን ህልውና ለመፈታተን የሚያደርገው ትንኮሳ ለማክሸፍ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማስፈለጉ ደም መለገሳቸውን ገልጸዋል።
ከደጀንነት ድጋፍ ባሻገር አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ እስከ ግንባር ድረስ ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በግዳጅ ላይ ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊት የደጀንነት ድጋፋቸውን ለመግለጽ ደም መለገሳቸውን የተናገሩት ደግሞ በጽህፈት ቤቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ተቋማት ዘርፍ ሃላፊ አቶ የኋላእሸት በቀለ ናቸው
በፈቃዳቸው የወር ደመወዛቸውን መለገሳቸውን አስታውሰው፤ እስከ ግንባር ድረስ ለመዝመትም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከአባላቱ ውስጥ በስንቅ ዝግጅት ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው ወይዘሮ ሶፊያ ኑሪ በሰጡት አስተያየት፤ በፓርቲው የሴቶች ሊግ አባላት ለመከላከያ ስንቅ በማዘጋጀት ሳይወስኑ በደም ልገሳው መሳተፋቸውን ገልጸዋል።