በሆሳዕና በግዳጅ ላይ ለተሰማራው ሠራዊት ስንቅ እየተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሆሳዕና በግዳጅ ላይ ለተሰማራው ሠራዊት ስንቅ እየተዘጋጀ ነው
ሆሳዕና ሐምሌ 21/2013 (ኢዜአ) በሐዲያ ዞን የሆሳዕና ከተማ ሴቶች በግዳጅ ላይ ለሚገኘ ው ሠራዊት ስንቅ እያዘጋጁ መሆናቸውን የዞኑ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ ወይዘሮ ስምረት ሳሙኤል ለኢዜአ እንዳሉት ሴቶች ለሀገር ክብርና ልዕልና ለቆሙት ልጆቻቸው ደጀንነታቸውን ለመግለጽ ስንቅ እያዘጋጁ ነው።
"ስንቁ በዋነኝት ዳቦ ቆሎ፣የእንጀራ ድርቆሽ፣ የገብስ ቆሎ፣ኩኪስና ደረቅ ምግብን ያካትታል" ብለዋል።
ሴቶች በሀገር ፍቅር ስሜት በመነሳሳት የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነትን ለሚያስከብረው ሠራዊት ስንቅ እያዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በስንቅ ዝግጅቱ ከተሳተፉ መካከል ወይዘሮ መሰረት መንግሥቴና ወይዘሮ እቴቱ ለማ በሰጡት አስተያየት የሀገሪቱን ህልውና ለማስከበር ለሚፋለመው ሠራዊት ስንቅ በማዘጋጀታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሠራዊቱ ግዳጁን እስኪወጣ ድረስ በደጀንነት ተሰልፈው አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
የዞኑ ሴቶች ቀደም ሲልም ለህልውና ዘመቻው 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጋቸው ታውቋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣የክልሎች ልዩ ኃይሎችና የአማራ ሚሊሺያ አሸባሪው የህወሓት ቡድን የከፈተውን ጦርነት እየተፋለሙ መሆኑ ይታወቃል።