የሸማቹንና የነጋዴውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከ1ሚሊዮን በላይ የመለኪያ መሣሪያዎች የትክክለኛነት ማረጋገጫ ተሰጠ፡፡ - ኢዜአ አማርኛ
የሸማቹንና የነጋዴውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከ1ሚሊዮን በላይ የመለኪያ መሣሪያዎች የትክክለኛነት ማረጋገጫ ተሰጠ፡፡
ሐምሌ 21/2013 (ኢዜአ) የህጋዊ ስነ ልክ መሳሪያዎችን ትክከለኛነት በማረጋገጥ የሸማቹንና የንግዱን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ በ2013 በጀት ዓመት ለ1ሚሊዮን 620ሺ180 ለሚሆኑ የመለኪያ መሣሪያዎች የትክክለኛነት ማረጋገጫ ተሰጥቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ ለ1ሚሊዮን 517ሺ427 የመለኪያ መሳሪያዎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ታቅዶ ለ1 ሚሊዮን 620ሺ180 የትክክለኛነት ማረጋገጫ ተስጥቷል፡፡
ከዚህ ውስጥ 358ሺ270 ልዩ ልዩ ሚዛኖችና የክብደት ማነፃጸሪያዎች፣204 የምድር ሚዛን፣ 1ሚሊዮን 162ሺ804 የርዝመት መለኪያዎች እና 98ሺ902 የፈሳሽ መለኪያዎች ይገኙበታል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የ2 ሽህ 680 የፈሳሽ ማጓጓዣ ቦቴዎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የታቀደ ሲሆን ለ2 ሽህ 781 ለሚሆኑት የትክክለኛነት ማረጋገጫ ተሰጥቷል፡፡
አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ የወጣላቸው የነዳጅ ሜትሮች፣ ሚዛኖች፣ የክብደት ማነፃፀሪያዎች እና የፈሳሽ መለኪያዎች ላይ ክትትል የተደረገ ሲሆን የጤናና የደህንነት መለኪያ መሳሪያዎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የአውቶ ቦቴ ቬሪፊኬሽን ማዕከልን ለማዘመን የሚያስችሉ ጥናቶች መካሄዳቸውንም የህጋዊ ስነ-ልክ ዳይሬክተር አቶ ያሬድ በፍቃዱ ተናግረዋል፡፡