ኢትዮጵያና አልጄሪያ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር ይሻሉ-- የአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና አልጄሪያ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር ይሻሉ-- የአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች
ሀምሌ 21/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና አልጄሪያ ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚሹ የአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአልጄሪያ አቻቸውን ራማታን ላማምራ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይታቸውም የአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራማታን ላማምራ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
ሁለቱ አገራት ከአፍሪካ ኅብረት ምሥረታ ጀምሮ በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ያሏቸውን ጠንካራ አቋም አሁንም ዳግም ማንጸባረቅ አለባቸው ብለዋል።
አገራቱ ታሪካዊና የረዥም ዓመት ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው ይህንን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወን እንዳለበት ተናግረዋል።
ከዚህም አንጻር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አልጀርስ በረራ እንዲያደርግ መጠየቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጠቁመዋል።
በቅርቡ ኢትዮጵያ ያካሄደችውን 6ኛው አገራዊ ምርጫ በስኬት መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ራማታን ላማምራ መናገራቸውን ተጠቅሷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው የአገራቱ ግንኙነት ይበልጥ ለመጠናከር ትኩረት እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
በዚህም ረገድ የሁለቱ አገራት የጋራ ኮሚሽኖች የኢትዮ- አልጀሪያ ግንኙነትን ይበልጥ በሚጠናከርበት ዙሪያ እንዲሰሩ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አልጀርስ በረራ እንዲጀምር እንሰራለን ማለታቸውንም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ያካሄዱት ውይይት የአገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር ያላቸውን የጋራ ፍላጎት እንደሚያመላክትም ነው አምባሳደር ዲና ያወሱት።
በሌላ በኩል በሕዳሴ ግድብ፣ በትግራይ ክልል ስለሚካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻና ስለ ኢትዮ-ሱዳን ድንበር ወቅታዊ ሁኔታ ለአልጄሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማብራሪያ መሰጠቱን አምባሳደር ዲና አስረድተዋል።