ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ ህወሃት በሚነዛው ሀሰተኛ ወሬ ሳይረበሽ ለህልውና ዘመቻው የድርሻውን ሊወጣ ይገባል - ምሁራን

ደሴ ሐምሌ 21/2013 (ኢዜአ ) ህብረተሰቡ ህወሓት በሚነዛው ሐሰተኛ ወሬ ሳይረበሽ የአካባቢውን ሰላም ተደራጅቶ በመጠበቅ ለህልውና ዘመቻው የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስገነዘቡ፡፡

"መንግስት ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን ለህዝቡ በማድረስ ውዥንብርን ሊቀንስ ይገባል" ሲሉም ምሁራኑ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አሰታውቀዋል ።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ይመር አሊ ለኢዜአ እንደገለፁት አሸባሪው የህወሓት ቡድን ጥርስ የነቀለበትን የሐሰት ወሬ ዛሬም አጠናክሮ በመቀጠል ህዝብን እያወናበደ ነው፡፡

አሸባሪው ያልተቆጣጠረውን አካባቢ ሁሉ ተቆጣጥሪያለሁ በማለት የትግራይን ህዝብ ብቻ ሳይሆን ሌላውንም ኢትዮጵያዊና የውጭ ሀገራት ጭምር እያወዛገበ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ህብረተሰቡ ከመንግስት የሚሰጠውን መረጃና ትዛዝ ብቻ በመቀበል የአካባቢውን ሰላም ተደራጅቶ በመጠበቅ ለህልውና ዘመቻው የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለማዳን መንግስት ያደረገው የክተት ጥሪ ተገቢ መሆኑን ጠቁመው "ህዝቡ በዘመቻው በሚኖረው ተሳትፎ  አቅም ያለው ብቻ ዘምቶ ሌላው ስነቅ አቀባይና ደጀን መሆን ይኖርበታል"፡፡

"ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች ሀገር ማስረከብ አሁን ያለነው ትውልድ ኃለፊነት ነው" ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ሁሉም የሚችለውን በማድረግ ከመከላከያና ፀጥታ መዋቅሩ ጎን መቆም እንዳለበት አመልክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የሰላም፣ ዲሞክራሲና ልማት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አልዩ ውዱ በበኩላቸው" ምላሱ ብቻ የቀረው አሸባሪው ህወሓት በሚነዛው የሐሰት ወሬ ህዝቡ ሳይደናገጥ አካባቢውን ነቅቶ መጠበቅና አጠራጣ ጉዳይ ሲመለከት ለመንግስት ጥቆማ መስጠት ይጠበቅበታል" ብለዋል።

ቡድኑ ህጻናትና አዛውንቶችን ሁሉ ወደ ጦር እየማገደ መሆኑ በዓለም አቀፍ ህግ እንደሚያስጠይቀው ጠቁመው "ኢትዮጵያዊያን የተቃጣብንን ጥቃት መክተን ለድል እንድንበቃ ሁሉም ከመንግስት ጎን መቆምና በህልውና ዘመቻው መሳተፍ አለበት" ብለዋል።

"መንግስትም ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን ለህዝቡ በማድረስ የሚፈጠረውን ውዝግብ መቀነስና ህዝቡ አደራጅቶ እንዲከላከል ማድረግ ይጠበቅበታል" ሲሉ አመልክተዋል።

እንደ ዶክተር አልዩ ገለጻ በሀገር ውጭና ውስጥ ያለ ሁሉም ኢትዮጵያዊያና የኢትዮጵያ ወዳጅ ሁሉ የውጭ ሀገር ጣልቃ ገብነትና ጫናን ለማቃለል እውነታውን ለዓለም ህዝብ ማሳወቅም ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም