የትግራይ ህዝብ የአሸባሪውን ሕወሃት እኩይ ዓላማ በማክሸፍ ከቡድኑ ራሱን ነጻ ሊያወጣ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ህዝብ የአሸባሪውን ሕወሃት እኩይ ዓላማ በማክሸፍ ከቡድኑ ራሱን ነጻ ሊያወጣ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሃምሌ 21/2013(ኢዜአ) የትግራይ ህዝብ ከመላ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሰለፍ የአሸባሪውን ህወሓት እኩይ ዓላማ በማክሸፍ ከቡድኑ ራሱን ነጻ ማውጣት እንዳለበት ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደና የኢትዮጵያውያን ተጋሩ ሲቪክ ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዮሃንስ ጎይቶም ጋር ቆይታ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ምክትል ሊቀ መንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ እንደገለጹት፤ "አሸባሪው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን ማተራመስ የጀመረው ዛሬ አይደለም"።
አሸባሪው ህወሓት ሲፈጠርም ኢትዮጵያን ለማተራመስ መሆኑን ገልጸው፤ ቡድኑ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ህዝቡን በዘርና በሃይማኖት በመከፋፈል የኢትዮጵያን ህልውና ሲፈታተን መቆየቱን አስታውሰዋል።
በተለይም የአማራና የኦሮሞ ብሔሮችን በማጋጨት የአገሪቷን ህልውና ለመፈታተን ሲያደርገው የቆየውን ሴራ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ሊከሽፍ መቻሉንም አንስተዋል።
እንደ ዶክተር ጫኔ ገለጻ፤ የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የማደግ፣ የመልማትና ከሌሎች ጋር በሰላም የመኖር ፍላጎት አለው።ይሁንና አሸባሪ ቡድኑ ህዝቡን ከወንድሞቹ ለመነጠል የጥላቻ ዘር ከመዝራት ባለፈ ዕድሜያቸው ለትምህርት እንጂ ለጦርነት ያልደረሱ ህጻናትና አቅመ ደካሞች ህይወታቸውን እንዲገብሩ እያደረገ ነው ብለዋል።
አሸባሪው ቡድን ገና ካሁኑ እርስ በእርሱ መከፋፈል መጀመሩን ጠቁመው፤ ይህም ክልሉን ስርዓት አልበኛ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
ንጹሃኑ የትግራይ ተወላጆች ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር የሽብር ቡድኑን እኩይ ዓላማ ታግሎ በማክሸፍ ነጻ መውጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
"የአሸባሪው ቡድን አገር የማተራመስ ሴራውን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይረዳል'' ያሉት ዶክተር ጫኔ፤ ምዕራባውያኑ ቡድኑ የሚፈጽመውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዳላዩ ማለፋቸው ያላቸውን ድብቅ የፖለቲካ ፍላጎት እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
ይህም ከቡድኑ አመራር አባላት ጋር የነበራቸውን የግንኙነት መስመር ለማስቀጠልና የኢትዮጵያን ልማት ለማስተጓጎል ያለመ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያውያን ተጋሩ ሲቪክ ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዮሃንስ ጎይቶም እንደሚሉት፤ አሸባሪው የህወሃት ቡድኑ ለትግራይ ህዝብ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ፣ አርሶ አደሩ ተረጋግቶ የእርሻ ስራውን እንዳያከናውን እንቅፋት ሆኗል።
"ኢትዮጵያ ለትግራይ ህዝብ ግዴታ ታስፈልጋለች" ያሉት አቶ ዮሃንስ፤ህዝቡ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ተነጥሎ መኖር እንደማይችል በመረዳት የሽብር ቡድኑ የሚፈጽማቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ማውገዝ እንዳለበት ጠቅሰዋል።
በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ ወጣቶች የአሸባሪው ህወሓትን ቡድን እስከመጨረሻው ለማጥፋት ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን መቆማቸውን በተግባር እያሳዩ ነው።