ቀጥታ፡

የሀገርን ህልውና ለማስከበር ተዘጋጅተናል- የደብረብርሀን ወጣቶች

ደብረ ብርሃን ሐምሌ 21/2013 (ኢዜአ) ሀገራዊ ጥሪ በመቀበል የሀገርን ህልውና ለማስከበር ተዘጋጅተናል ሲሉ የደብረብርሀን ከተማ ወጣቶች ገለጹ። 

የደብረብርሃን ከተማ ነዋሪዎች መከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ሀይልና ሚሊሻውን የደገፉበትንና አሸባሪውን ህወሃት ያወገዙበትን ህዝባዊ ሰልፍ ዛሬ አካሂዷል።

ነዋሪዎቹ  ጁንታው የኢትዮጵያ ነቀርሳ በመሆኑ ከመላው ህዝብ ጋር በመተባበር እንነቅለዋለን፤ የኢትዮጵያ ትንሳኤ በሴራ አይደናቀፍም የሚሉና መሰል  መፈክሮችን በማስተጋባት አሸባሪውን ህወሃት አውግዘዋል።

መከላከያ ሰራዊት ፣ ልዩ ሀይልና ሚሊሻ የሀገርን ክብር ለማስጠበቅ እያደረጉ ስላለው ተጋድሎም አጋርነታቸውን ገልጸዋል።

በሰልፉ የተሳተፉ ወጣቶችም ሀገራዊ ጥሪን ተቀብለው መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል በህልውና ዘመቻው ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን ለኢዜአ አስታውቀዋል ።

ከወጣቶቹ መካከል ሰለሞን አረጋኸኝ እንደገለጸው ህወሃት የሀገርን የማፍረስ አላማውን ለማሳካት ህዝብን በዘርና በሃይማኖት በመከፋፈል ለግጭት ሲዳርግ ቆይቷል።

ቡድኑ ለ27 አመት የፈጸመው ግፍ አልበቃ ብሎት አሁን ላይ ከውጭ ጠላቶች ጋር በመተባበር የሀገርን ህልውና ለመድፈር ትንኮሳውን መቀጠሉን አመልክቷል።

መንግስት ሀገር ለማፍረስ የተነሳውን የአሸባሪ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማሶገድ ያቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ በመቀበል በህልውና ዘመቻው ለመሳፍ መዘጋጀቱን ገልጻል።

"ከሃዲውን ቡድን ለመደምሰስ የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ በመቀበል ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ለመቀላቀል ተዘጋጅቻለሁ" ያለው ደግሞ ወጣት ሽመልስ አጋዥ ነው።

ከመከላከያ ሰራዊት ፣ ልዩ ሀይልና ሚሊሻ ጎን በመሰለፍ የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር በሙሉ ወኔ መነሳሳቱን ገልጿል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃድቅ በሰልፉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት "ከአባቶቻችን የወረስነው  አብሮነትን፣ አንድነትንና ለሰው ልጅ ክብር መስጠትን ነው " ብለዋል።

"የወረስነውን መልካም እሴት ትውልዱ እንዲያስቀጥል ከመከላከያ ሰራዊታችን ጎን ተሰልፈን የህወሃትን ቡድን በግንባር በመፋለም የሀገሪቱን ትንሳኤ እናበስራለን"  ሲሉም ተናግረዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን  ለ27 ዓመት የዜጎችን የአብሮነት እሴት በመሸርሸር ሀገርን  ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኪሳራ  መዳረጉን አመልክተዋል ።

"ቡድኑ አሁን ላይ  በንፁሃን ዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ግፍ በተባበረ ክንድ ማስቆም የግድ ይላል" ያሉት ዋና አስተዳዳሪው መላው ህዝብ  ለሀገር ህልውና ዘመቻው የጀመረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። 

የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ በበኩላቸው "ህዝቡ በህወሃት የተከፈተበትን ጦርነት ለመመከት በህልውና ዘመቻው ለመሳተፍ እያደረገ ካለው እንቅስቃሴ በተጓዳኝ አካባቢውን ነቅቶ መጠበቅ አለበት" ብለዋል።

"ህወሃት አማራን በማዳከም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የጀመረውን የጦርነት ዘመቻ ወጣቱ የፀጥታ ሃይሉን በመቀላቀል ትውልዳዊ አደራውን ሊወጣ ይገባል"  ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም