ወታደራዊ መኮንኖቹ የህዳሴው ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸው እንደማይቋረጥ አረጋገጡ - ኢዜአ አማርኛ
ወታደራዊ መኮንኖቹ የህዳሴው ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸው እንደማይቋረጥ አረጋገጡ
ድሬዳዋ ሐምሌ 21 /2013(ኢዜአ) የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከመጠበቅ ባሻገር ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የሁርሶ ኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ወታደራዊ አመራሮች ገለጹ፡፡
አመራሮቹ ለኢዜአ እንዳስታወቁት የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባልነታቸው ከሚጠበቅባቸው የሙያ ግዴታ በተጨማሪ ለግድቡ ግንባታ የገንዘብ አስተዋጽኦ ድጋፋቸውን ያጠናክራሉ፡፡
በቅርቡ የተበሰረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ከማስደሰቱም በላይ፤በገንዘብ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክር አነሳስቶታል፡፡
በትምህርት ቤቱ የ3ተኛ ብርጌድ 3ተኛ ሻለቃ ምክትል አዛዥ ሻለቃ ሺፈራው ሽብሩ
የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እስኪሰጥ ድረስ ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
" የግድቡ ምልክት የሆነው ዋንጫ ድሬዳዋ መግባቱ ድጋፋችንን ለማጠናከር ያስችለናል" ብለዋል፡፡
"ግድቡ የማንነታችን፣ የህልውናችንና የህይወታችን መሠረት ነው" ያሉት ደግሞ የትምህርት ቤቱ አሰልጣኝ መቶ አለቃ ካሊድ ዩሱፍ ናቸው፡፡
ግድቡን እንደ ዓይናቸው ብሌን ከመጠበቅ ባሻገር አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ግንባታውን ዳር እንደሚያደርሱ ተናግረዋል፡፡
የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ከድሬዳዋ ወደ ትምህርት ቤቱ በሚመጣበት ወቅት ሠራዊቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
የትምህርት ቤቱ የ2ተኛ ብርጌድ 3ተኛ ሻለቃ አዛዥ ሻለቃ ታምራት በደቾ በበኩላቸው "በሙያዬ የግድቡን ጥበቃ፣ በዜግነቴ ደግሞ የገንዘብ አስተዋጽኦ በማድረግ የተፈጥሮ ሃብታችንን የመጠቀም መብታችንን አስከብራለሁ" ብለዋል፡፡
"ሠራዊቱ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፌን አላቋርጥም በማለት አቋም ይዟል " ያሉት ደግሞ በማስልጠኛው የሰልፍ ዴስክ አስተባባሪ ሻምበል አክሊሉ ለገሰ ናቸው።
መኮንኖቹ ሠራዊቱ የ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም መጠናቀቅንና የህዳሴ ግድብ 2ተኛ ዙር ውሃ ሙሌት በስኬት መሞላቱ የፈጠረውን ደስታ በመግለጽ በሙሌቱ የተገኘው ድል ወደ ኃይል ማመንጨት እንዲያድግ በሚደረገው ጥረት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ፀሐፊ አቶ ገበየሁ ወጋየሁ በቅርቡ ድሬዳዋ የገባው የግድቡ ዋንጫ ወደ ትምህርት ቤቱ ተልኮ ድጋፍ ለማሰባሰብ ዕቅድ መያዙን ለኢዜአ አስታውቀዋል።