በጋሞና ቤንች ሸኮ ዞኖች በአንድ ቀን ጀምበር ከ20 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተተከለ - ኢዜአ አማርኛ
በጋሞና ቤንች ሸኮ ዞኖች በአንድ ቀን ጀምበር ከ20 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተተከለ
አርባ ምንጭ፣ (ሚዛን) ሐምሌ 21/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል በጋሞና በቤንች ሸኮ ዞኖች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአንድ ቀን ጀምበር ከ20 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተተከለ።
በጋሞ ዞን በተካሄደ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለና ከ200 በላይ የፓርላማ ሴቶች ኮከስ አባላት በመሳተፍ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
በተጨማሪም በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደም አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
በጋሞ ዞን ህብረተሰቡና የመንግስት አካላት በተገኙበት በ14 ወረዳዎችና 6 የከተማ አስተዳደሮች በተካሄደው ችግኝ ተከላ ከ10 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተተክሏል።
ምክትል አፈ-ጉባኤዋ በወቅቱ እንዳሉት ከዚህ ቀደም በተከታታይ ዓመታት በተተከሉ ችግኞች የተራቆቱ መሬቶች በአረንጓዴ እየተሸፈኑ መጥተዋል።
"የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስነምህዳርን በመጠበቅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አስተዋጽኦው የጎ በመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል።
በተለይ የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋን ለመከላከል የሚያስችል በመሆኑ ህዝቡ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ የበኩሉን እንዲወጣ ነው ወይዘሮ ሽታዬ ጥሪ ያቀረቡት።
ከችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ተሳተፊዎች መካከል የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው "አረንጓዴ አሻራን በማጠናከር ለቀጣይ ትውልድ የለመለመች ኢትዮጵያን ማውረስ ይገባል" ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው አረንጓዴ አሻራ እንዲሳካ በጋሞ እና ጎፋ ዞኖች ባሉ ስምንት የችግኝ ጣቢያዎች ከ1 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በማፍላት ለህብረተሰቡ እያሰራጨ መሆኑንም ገልጸዋል።
ተቋሙ በትናንትናው ዕለት ከ30 ሺህ በላይ፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ከ100 ሺህ በላይ ችግኞችን መትከሉን ተናግረዋል።
በትናንትናው ዕለት በጋሞ ዞን 10 ሚሊዮን ችግኝ መተከሉን የገለጹት ደግሞ የዞኑ አካባቢ ጥበቃና ደን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ማዜ ሸቀነ ናቸው።
ሀላፊው እንዳሉት ባለፉት ሦስት ዓመታት ለአረንጓዴ ልማት በተሰጠው ትኩረት የዞኑን የደን ሽፋን ከ19 በመቶ ወደ 26 በመቶ ማሳደግ ተችሏል።
በተመሳሳይ ዜና በቤንች ሸኮ ዞን በአንድ ጀንበር 10 ሚሊዮን ችግኝ መተከሉን በሰሜን ቤንች ወረዳ አረንጓዴ አሻራቸውን ያሳረፉት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ቀበሌ መንገሻ ገልጸዋል።
ለችግኝ ተከላ ስራው ከአካባቢ ጥበቃና እርሻ ጋር በመናበብ በቂ የመትከያ ቦታ አስቀድሞ እንዲዘጋጅ መደረጉን ጠቁመዋል።
የዞኑ አካባቢ ጥበቃ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ውቢት ገምታ ትናንት በአንድ ጀምበር የተተከለውን ጨምሮ በተያዘው የክረምት ወራት 69 ሚሊዮን ችግኝ በዞኑ እንደሚተከል ገልጸዋል።
ችግኝ የሚተከልባቸው ተቋማት ጋር በመዋዋል ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ተንከባክቦ ማጽደቅ ላይ የተደራጀ ሥራ እንደሚሰራም ነው የጠቆሙት።
የዞኑ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ በበኩላቸው ችግኞች ሙያዊ መስፈርት ጠብቀው እንዲተከሉ ባለሙያዎች በሁሉም ወረዳና ቀበሌዎች እንዲሰማሩ መደረጉን ተናግረዋል።
በችግኝ ተከላ ስነ ስርአቱ ላይ ከተሳተፉት መካከል አቶ አሸናፊ ንጉሴ ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበስ ተግባር በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውንና በቀጣይም ችግኞችን እንደሚንከባከቡ ተናግረዋል ።
በደቡብ ክልል በአንድ ቀን ጀንበር ኢትዮጵያን የማልበስ መርሃ ግብር 80 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል መታቀዱ ታውቋል።