ቀጥታ፡

የባሌ ዞን የመንግስት ሠራተኞችና አመራሮች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደም ለገሱ

ጎባ ፤ ሐምሌ 20/2013(ኢዜአ) የባሌ ዞን ሴክተር መስሪያ ቤቶች ሠራተኞችና አመራሮች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደም በመለገስ አጋርነታቸውን ገለጹ።
ሠራተኞቹና አመራሮቹ ዛሬ ደም የለገሱት “ደማችን ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን” በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀ መርሃ ግብር ላይ ነው፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ከተሳተፉት መካከል የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ባለሙያ ወይዘሮ አስቴር መኮንን "የሀገር ሉአላዊነት ለማስከበር ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈለ ላለው የመከላከያ ሠራዊት ደሜን በመለገሴ ክብር ይሰማኛል" ብለዋል፡፡

በቀጣይም ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ በሁሉም ዘርፍ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን እንደሚሆኑ ቃል በመግባት አረጋግጠዋል፡፡

"የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር በሚደረገው ማንኛውም ሀገራዊ ጥሪና የድጋፍ ሥራ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን መሆኔን ለመግለጽ ደሜን በተነሳሽነት ሰጥቻለሁ" ያሉት ደግሞ የዞኑ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ባለሙያ አቶ ዩሱፍ መሐመድ ናቸው፡፡

ለሀገር ህልውና እየተዋደቀ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የአካባቢያቸውን ሴቶችና ወጣቶች በማስተባበር  እየተደረገ ያለውን ድጋፍ ለማስቀጠል እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ቱጁባ በበኩላቸው ፤በክረምቱ ሁለት ወራት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በዞኑ ከ1ሺህ 500 በላይ ዩኒት ደም ለማሰባሰብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለሀገር ሉዓላዊነት እየተዋደቀ ለሚገኘው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት የሚደረገው የደም ልገሳም የእዚሁ ጥረት አካል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የባሌ ዞን የፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰይፈዲን ሀሰንም "የዞኑ ማህበረሰብ በአሁኑ ወቅት ገንዘብ በማሰባሰብ፣ ሰንጋዎች እና በጎችን በማዋጣት እንዲሁም በሌሎችም የድጋፍ ስራዎች ለመከላከያ ሠራዊታችን ያለውን አለኝታነት በቁርጠኝነት እያሳየ ይገኛል" ብለዋል፡፡

በዞኑ በሚዘጋጁ የተለያዩ መድረኮች ህብረተሰቡ በተለያዩ መንገዶች ሠራዊቱን ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት እየገለጸ መሆኑን ጠቁመው፤ በዞኑ ሠራተኞችና አመራሮች የተጀመረው የደም ልገሳ እስከ ታችኛው የህብረሰብ ክፍል እንደሚወርድ አስታውቀዋል።
ኃላፊው እንዳሉት፤ በሀገር ህልውና ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመመከት የህይወት መስዋዕትነትን እየከፈለ ያለውን የመከላከያ ሠራዊት መደገፍ ሀገራዊ ግዴታ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የዜግነት ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም