ቀጥታ፡

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ መቀሌ ከተማን ለማሰልጠን ውል ተፈረራመ

አዲስ አበባ ሀምሌ 2/2010 አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከመቀሌ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ጋር የሁለት ዓመት የኮንትራት ውል በመፈራረም ስራውን በይፋ ጀመረ። መቀሌ ከተማ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ከአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ጋር ከተለያየ በኋላ አሰልጣኝ ሲያፈላልግ የቆየ ሲሆን ገብረመድህን ኃይሌን አሰልጣኝ አድርጎ ለመቅጠር በቃል ደረጃ ተስማምቶ እንደነበር ይታወቃል። የክለቡ የወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ለአከ ገብረህይወት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ዛሬ በመቀሌ በተካሄደ የፊርማ ስነ-ስርዓት ገብረመድህን ኃይሌ በክለቡ ለሁለት ዓመት የሚያቆየውን ፊርማ አኑሯል። መቀሌ ከተማ አሰልጣኙን የሾመበት ዋነኛው ምክንያት ክለቡ ኳስን መሰረት ያደረገ የአጨዋወት ስልት እንዲኖረውና ተተኪ ተጫዋቾችን በማፍራት ቡድኑን ማጠናከርን ታሳቢ አድርጎ እንደሆነ ተናግረዋል። በስምምነቱ መሰረት በክለቡ ሁለተኛ ቡድን የሚገኙ ታዳጊ ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን በማሳደግ እንደሚያጫውትም ገልጸዋል። ክለቡ ከአሰልጣኝ ሹመቱ በተጨማሪ በቀጣይ ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ ሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን እንዳስፈረመና የአራት ነባር ተጫዋቾችን ውል እንዳደሰም ነው አቶ ለአከ ያስረዱት። አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በዘንድሮው ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጅማ አባጅፋርን በመያዝ ሻምፒዮን መሆኑ የሚታወስ ነው። ገብረመድህን ኃይሌ ትራንስ ኢትዮጵያ፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ መድን፣ ቡና፣ ደደቢት፣ መከላከያና ጅማ አባቡና ክለቦችን አሰልጥኗል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም