ቀጥታ፡

ህዝቡ አንድነቱን በማጠናከር ለመከላከያ ሰራዊትና ልዩ ሀይሎች ድጋፍ እንዲያደርግ አቶ ኦርዲን በድሪ ጥሪ አቀረቡ

ሐረር (ኢዜአ) ሐምሌ 20 ቀን 2013 ህዝቡ አንድነቱን በማጠናከር ለመከላከያ ሠራዊትና ለክልል የፀጥታ አካላት ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን ሊያረጋግጥ ይገባል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ጥሪ አቀረቡ ።

የሐረሪ ክልል ነዋሪዎች የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የደገፉበትንና  አሸባሪው ህወሓትን ያወገዙበትን  ታላቅ ህዝባዊ ሰልፍ ዛሬ አካሂደዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በሰልፉ ላይ ባደረጉት ንግግር የህውሓት የጥፋት ቡድን መንግስት ያወጀውን የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት ለእኩይ ተግባሩ በመጠቀም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ትንኮሳና የሽብር ተግባር እየፈጸመ ነው። 
"አሸባሪው ቡድን ህጻናትና እናቶችን ጭምር ለጦርነት መማገዱ እንደወትሮው ለስልጣን እንጂ ለህዝብና ለሀገር ግድ እንደሌለው በተግባር ያረጋገጠበት ነው" ብለዋል።

"ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ያፀኗት ሀገራችን በከሀዲዎች እንደማትበታተንና ለየትኛውም ሀይል እንደማትንበረከክ በሚያስተምር መልኩ ጁንታውን በመደምሰስ እስከ መጨረሻ እልባት መስጠት ያስፈልጋል"። ሲሉም ተናግረዋል።
መላው ህዝብ አንድነቱን በማጠናከር የሀገርን ህልውና ለማስከበር ከአሸባሪው ህውሀት ጋር እየተፋለመ ላለው ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና ለክልል የፀጥታ አካላት ድጋፍ  በማድረግ አጋርነቱን በተግባር ማረጋገጥ እንዳለበት"  ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ መንግስትና ህዝብ ሠራዊቱ ህግን ለማስከበርና ፀረ-ሠላም በሆነው የህወሓት ቡድን ላይ ለሚወስዳቸው እርምጃዎች የጀመረውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል የቀድሞ ጦር ሠራዊት አባል ሻለቃ ከበደ መርጋ "ለሀገር ሉአላዊነት እና ለዜጎች ክብር በጀግንነት እየተዋደቀ ላለው የመከላከያ ሠራዊት ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ከህብረተሰቡ ድጋፍ ከማሰባሰብ ጀምሮ በግንባር ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ ጁንታውን ለመደምሰስ ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
"የመከላከያ ሠራዊት ውለታ ተከፍሎ አያልቅም"  ያሉት ደግሞ  አቶ መሀመድ አብዶሽ ናቸው።  

"የኢትዮጵያን ክብር አሳልፎ የሚሰጥ ትውልድ የለም"  ያሉት አቶ መሀመድ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ የህወሓት ጁንታ ቡድንን ለማሶገድ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሽብርተኛውን ህወሓት ለመደምሰስ በሚደረገው ዘመቻ ላይ ከሠራዊቱ ጎን ለመቆም ለመዝመት መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ መቶ አለቃ ወንድሙ ኩራ ናቸው።

አሁን ላይ  በአካባቢያቸው የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

በእለቱ ከተደረገው ሰልፍ በተጨማሪ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የደም ልገሳ ተደርጓል።
በሰልፉ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች እንዲሁም በክልሉ ከገጠርና ከተማ የመጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም