ቀጥታ፡

የምርጫው አጠቃላይ ሂደት የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ ግንባታ አንድ እርምጃ ወደ ፊት የወሰደ ነው - ምሁራን

ሀምሌ 20/2013 (ኢዜአ) የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ አጠቃላይ ሂደት የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ ግንባታ አንድ እርምጃ ወደ ፊት የወሰደ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ።

ተቋማት በምርጫው ሂደት ላይ ያሳዩት ቁርጠኝነትም ለቀጣይ አገራዊ ሥራዎች ትምህርት የሰጡ መሆናቸውንም ነው ያነሱት።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት የሚዘጋጀው የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ "ዴሞክራሲ አንድ እርምጃ፤ የስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ ምልከታዎች" በሚል ርእሰ ሃሳብ ውይይት አካሄዷል።

ውይይቱም ለአገር ህልውና ዋጋ እየከፈለ ላለው የአገር መከላከያ ሠራዊት ክብር በመስጠት ነው የተጀመረው።

በመድረኩም በምርጫው ሂደት ላይ የባለድርሻ ተቋማት፣ የመገናኛ ብዙሃንና የሲቪክ ማህበራት የነበራቸው ሚና ላይ የውይይት የመነሻ ሃሰብ ቀርቧል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ በዚህን ወቅት እንደገለጹት፤ ምርጫውን የሚመለከቱ ህግና አዋጆች ማውጣት እንዲሁም አስፈጻሚ አካላትን የመሰየሙ ስራ አሳታፊ ነበር።

የፖለቲካ አመራሩም ምርጫውን ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ ለማድረግ ቁርጠኛ ሆኖ መስራቱን ነው ያነሱት።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተቋቁሞ በሂደቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሄደበትን ርቀት አድንቀዋል።

ይህም ምርጫው ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ ምርጫዎች በብዙ መልኩ የተሻለ እንዲሆን ከማድረጉም ባሻገር ለኢትዮጵያ ቀጣይ የዴሞክራሲ ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ተናግረዋል።

ብሔራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ቶላ በበኩላቸው፤ መንግስት ምርጫውን ሰለማዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን ብሔራዊ ግብረ ሃይል አቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ግብረ ሃይሉ ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ አሰራር በመዘርጋት የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑንም ነው የገለጹት።

የጸጥታ መዋቅሩ ከየትኛውም የፖለቲካ ውግንና ነጻ በሆነ መልኩ ለምርጫው ሰላማዊነት መስራቱን ያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህም ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን የራሱን በጎ ሚና ተጫውቷል ነው ያሉት።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ተሰባስበው ችግሮቻቸውን ለመፍታት የሄዱበት ርቀት የዘንድሮውን ምርጫ ከሌሎች ምርጫዎች የተለየ እንዳደረገው የገለጹት ደግሞ የደስትኒ ኢትዮጵያ መስራችና የማይንድ ኢትዮጵያ አባል ዶክተር ንጉሱ አክሊሉ ናቸው።

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የምርጫ ቦርድ የመሳሰሉ የዴሞክራሲ ተቋማት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገነቡበትን ሂደት አድንቀው፤ በቀጣይ የተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች  ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት ከድህረ ምርጫ በኋላ ባሉ ጉዳዮች ላይም አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸው፤ ማይንድ ኢትዮጵያ መሰል ውይይቶችን ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፤ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ከውስጥም ከውጭም ሆነው ለማደናቀፍ ሲሰሩ የነበሩ ሃይሎች መኖራቸውን አስታውሰዋል።

ነገር ግን በአገር ውስጥ ያሉ የግልም ሆኑ የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ውግንናቸውን ለኢትዮጵያ በማድረግ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ሰርተዋል ነው ያሉት።

መገናኛ ብዙሃን ከድህረ ምርጫ በኋላ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚደረጉ ጥረቶችን በመመከት ረገድም ጉልህ ሚና እያበረከቱ እንደሚገኙም ነው ያነሱት።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም ምርጫው የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ግንባታ አንድ እርምጃ ወደ ፊት የወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።

"ምርጫው የጸጥታ ችግር ይገጥመዋል" የሚል ስጋት እንደነበር አስታውሰው ፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለምርጫው ሰላማዊነት በብርቱ መስራታቸው የጸጥታ ችግር ሳይከሰት ምርጫውን ማከናወን ማቻሉን ጠቅሰዋል።

ለዚህም "ኢትዮጵያውያን ምስጋና ይገባቸዋል ነው" ያሉት።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ሂደት ሰላማዊነት ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም