ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊያን ለሀገራዊ ጥሪው እየሰጡ ያለው ምላሽ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት--- መከላከያ ሚኒስቴር

ደሴ ሐምሌ 20/2013 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት የተከፈተውን ጦርነት በአጭር ጊዜ በድል ለማጠናቀቅ በሀገር ውስጥም ሆን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የጀመሩትን ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያጠናክሩ መከላከያ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በደሴ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የመከላከያ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ፍስሃ ወልደሰንበት እንዳሉት  ኢትዮጵያ  በህብረተሰቡ አንድነትና የተባበረ ክንድ የሚገጥሟትን ፈተናዎች በድል ትወጣለች።

የኢትዮጵያን ጥንካሬና አንድነት የማይሹ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ህዝብን በእምነትና በቋንቋ ከፋፍለው እርስ በእርስ ለማጫረስ የሚያደርጉት ጥረት እየከሸፈ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ የህዳሴው ግድብ ግንባታና 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌትን ለማስተጓጎል እንዲሁም 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማደናቀፍ ያልተደረገ ሙከራ እንዳልነበር አቶ ፍሰሀ አስታውሰዋል።

"የህግ ማስከበር ዘመቻውን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ለመጠምዘዝ ሌት ተቀን እየሰሩ ያሉ ታሪካዊ ጠላቶች ቢኖሩም ኢትዮጵያ በህዝቡ አንድነትና የተባበረ ክንድ ፈተናዎቿን በሙሉ በድል አድራጊነት እየተወጣች ትገኛለች" ብለዋል።

አሁን ላይ አሸባሪውና የእናት ጡት ነካሹ ህወሓት የከፈተውን ጦርነት በአጭር ጊዜ በድል ለማጠናቀቅ በውስጥም ሆን በውጭ ሀገር የሚኖሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጀመሩትን ሁለተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ህዝቡ ከጫፍ እስከ ጫፍ ለመከላከያ ሠራዊቱ ያደረገው ሁለተናዊ ድጋፍ ለሠራዊቱና ለፀጥታ አባላት ብርታትና ኃይል እንደሆነው ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።

"በወሎ በኩል የተጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ ወሳኝ በመሆኑ ተረባርበን አሸባሪውን ቡድን መቅበር ይጠበቅብናል" ሲሉም በአጽእኖት ተናግረዋል።

በየጊዜው ለማንኛውም የሀገር ጥሪ ኢትዮጵያ በልጆቿ አፍራ እንደማታወቅ ታሪክ ምስክር መሆኑን የጠቆሙት አቶ ፍሰሃ ህዝቡ ለአሁኑ የህልውና ዘመቻ ከቁስ ባለፈ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመከፍል ያሳየው ቁርጠኝነት የሚደነቅና ጠላትን ያሳፈረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዘመቻውን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ወደ ልማት ለመዞር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከመከላከያ ሠራዊቱና ፀጥታ መዋቅሩ ጎን በመሰለፍ ደጀንነቱን ማረጋገጥና የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ በበኩላቸው እንዳሉት የዞኑ ህዝብ ለህልውና ዘመቻው ከሚያደርገው ድጋፍ ባለፈ ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ አጋርነቱን በተግባር እያሳየ ነው፡፡

"አሸባሪው ቡድን ለኢትዮጵያ ቀርቶ አለሁልህ ለሚለው ለትግራይ ህዝብ እንኳ እንደማይጠቅም መሰረተ ልማቶችን ማውደሙና እርዳታ እንዳይደርስ ማደናቀፉ አንድ ማሳያ ነው" ብለዋል፣

"ህወሓት ነፍስ ያላወቁ ህጻናትን ወደ ጦርነት እየማገደ እናቶችን የወላድ መካን በማድረግ ታሪካዊ ጠላትነቱን በግልጽ እያሳየ የሚገኝ የክፉ አውሬ ቡድን ስብስብ ነው" ሲሉም ገልጸውታል።

 የትግራይ ህዝብ ቡድኑን በቃህ በማለት ከኢትዮጵያ ወንድምና እህት ህዝብ ጋር ተሰልፎ የጥፋት ድርጊቱ እንዲቆም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

''የወሎ ህዝብ ለፍቅርና ለአብሮነት እንጅ ለጠብና ሁከት አይመችም'' ያሉት አስተዳዳሪው ህዝቡ ሀገር ለማፍረስ የመጣን ቡድን ላይመለስ ለመቅበር እስከ ህይወት መስዋትነት ለመክፈል ቆርጦ መነሳቱን ተናግረዋል።

ከመቅደላ ወረዳ የመጣችው ወጣት ሀይማኖት ብርሌው በሰጠችው አስተያየት ሀገር በማፍረስ ተግባር የተሰማራውን የህወሓት ቡድን ለመደምሰስ ወደ ግንባር ለመሄድ መወሰኗን ገልፃለች።

''ዳር ድንበሯ ተከብሮ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች ሀገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ የአባቶቻችንን ታሪክ መድገም አለብን'' ያለቸው ወጣቷ በህልውና ዘመቻው ሁሉም የሚችለውን በማድረግ ሀገረን ማዳን እንዳለበት ተናግራለች።

የአካባቢውን ወጣት በማስተባበር የመንግስትን የክተት ጥሪ ተቀብለው ወደ ግንባር ለመዝመት እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቁማለች።

በውይይቱ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የፀጥታ አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም