በምስራቅ ሸዋ ዞን 294 ተፋሰሶችን መሰረት ያደረገ የጎርፍ የመከላከል ሥራ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ሸዋ ዞን 294 ተፋሰሶችን መሰረት ያደረገ የጎርፍ የመከላከል ሥራ እየተካሄደ ነው
አዳማ ሐምሌ 20/201 (ኢዜአ) በምስራቅ ሸዋ ዞን በህዝብ ተሳትፎ 294 ተፋሰሶችን መሰረት ያደረገ የጎርፍ መከላከል ሥራ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ ለኢዜአ እንደገለጹት የክረምት ወቅትን ተከትሎ ሊከሰት የሚችል የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
በዞኑ በሚገኙ አስር ወረዳዎች 294 ተፋሰሶች ተለይተው ህብረተሰቡን በማሳተፍ የጎርፍ መከላከል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።
ከስራዎቹ መካከል የእርከንና በከተሞች አካባቢ የጎርፍና ፍሳሽ መውረጃ ቦዮችን ማፅዳት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ህብረተሰቡ ሊከሰት ከሚችለው ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ራሱን እንዲጠብቅና ችግሮች ከተከሰቱም አደጋውን ለመቋቋም የሚያስችል ሥራ እየከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ በምስራቅ ሸዋ ዞን የአዋሽ ወንዝን ተከትሎ ባሉ ፈንታሌ፣ ቦሶት፣ አዳማ፣ ሉሜ፣ ቦራ፣ ዱግዳና ሊበን ወረዳዎች ህብረተሰቡ በክረምቱ ሊከሰት ከሚችል የጎርፍ አደጋ አስቀድሞ እንዲጠነቀቅ በየደረጀው ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አቶ መስፍን አስረድተዋል።
በተፋሰሶች ላይ እየተሰራ ካለው የእርከን ማሰር ሥራ ጎን ለጎን የተራቆቱ መሬቶች ላይ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ የማልበስ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
"በተደጋጋሚ ለጎርፍ በሚጋለጡ አዳማ፣ ፋንታሌ፣ ቦሰትና መተሃራ ከተሞች ህብረተሰቡ ከድንገተኛ ጎርፍ ራሱን እንዲጠብቅ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች ከክልሉ መንግስት በተሰጠ አቅጣጫ መሰረት እየተከናወኑ ነው" ብለዋል።
አምና የአዋሽ ውንዝ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ከ3ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውንና በርካታ ቤቶች መውደማቸውን የገለጹት የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ ዘንድሮ ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት ተከታታይ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
በከተሞች ነዋሪዎች የተደፈኑ የፍሳሽና ጎርፍ መውረጃ ቱቦዎችን እንዲያፀዱ በማድረግ በኩል የተሻሉ ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።