በገንዘብ፣ በጉልበትና ግንባር ድረስ በመዝመት ከሠራዊቱ ጎን መቆም እንሻለን - በሥንቅ ዝግጅት የሚሳተፉ ሴቶች - ኢዜአ አማርኛ
በገንዘብ፣ በጉልበትና ግንባር ድረስ በመዝመት ከሠራዊቱ ጎን መቆም እንሻለን - በሥንቅ ዝግጅት የሚሳተፉ ሴቶች
ሐምሌ 20 2013(ኢዜአ) በገንዘብ፣ በጉልበትና ግንባር ድረስ በመዝመት ከመከላከያ ሠራዊት ጎን መቆም እንደሚሹ በአዲስ አበባ ከተማ በሠራዊቱ ሥንቅ ዝግጅት ላይ የሚሳተፉ ሴቶች ገለጹ።
በአዲስ አበባ የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ሴቶች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ስንቅ አዘጋጅተዋል።
ለመከላከያ ሠራዊቱ የተደረገው የስንቅ ዝግጅት በክፍለ ከተማው ሴቶች አደረጃጀት አስተባባሪነት የተዘጋጀ ነው።
የክፍለ ከተማው ሴቶች ከስንቅ ዝግጅት ባሻገር ግንባር ድረስ በመሄድ ሠራዊቱን ለማበረታታትና በሚችሉት ሁሉ ከጎኑ ለመሰለፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
በስንቅ ዝግጅቱ የተሳተፉት ወይዘሮ እታፈራሁ ወይዳናው በሰጡት አስተያየት በገንዘብ፣ በጉልበትና ግንባር ድረስ በመዝመት ከሠራዊቱ ጎን መቆም እንደሚሹ ተናግረዋል።
"የትግራይ ሕዝብ ወንድማችን ነው፣ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሕጻናትን ለጦርነት እየማገደ መሆኑን እናወግዛለን" ብለዋል።
በልበሙሉነት ከሠራዊቱ ጎን ለመሰለፍ እየዘመቱ ያሉ ወጣቶችን እንደሚያበረታቱም ነው የገለጹት።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ አስናቀች ምስጋኑ ሴቶች ባላቸው አቅም በማዋጣት ስንቅ እያዘጋጁ መሆኑንና በቀጣይ ለመዝመት ጭምር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የክፍለ ከተማው ብልጽግና የሴቶች ሊግ ኃላፊ ወይዘሮ ይታይሽ ደነቀው በበኩላቸው ሴቶች በከፍተኛ ተነሳሽነት ለሠራዊቱ ስንቅ እያዘጋጁ መሆኑን አንስተው በመጀመሪያው ዙር ከ250 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው ስንቅ ለሠራዊቱ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ከስንቅ ዝግጅት ባሻገርም ባሎቻቸው፣ ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው ከሠራዊቱ ጋር እንዲቀላሉ እያበረታቱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
የአገር መከላከያ ሠራዊቱ በሰው ኃይል እንዲጠናከር የበኩላችንን እንወጣለን ያሉት ወይዘሮ ይታይሽ የክፍለ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔዋ ሠራዊቱን መቀላቀላቸውን ለአብነት ጠቅሰዋው ሴቶች ከሠራዊቱ ጎን ለመሰለፍ መነቃቃታቸውንና ቁርጠኞች እንደሆኑም ነው የገለጹት።