ኢትዮጵያና ጃፓን የ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ስምምነቶችን ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ጃፓን የ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ስምምነቶችን ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 20/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያና የጃፓን መንግሥታት የ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እና የዕዳ ክፍያ ጊዜ ማራዘሚያ ስምምነቶችን ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሃብረቢ እና በኢትዮጵያ የጃፓን ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ዛሬ ተፈራርመዋል።
የመጀመሪያው ስምምነት ለምግብ አቅርቦት መርሃ-ግብር የሚውል የ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ120 ሚሊዮን ብር ሲሆን በስምምነቱም 3 ሺህ 300 ቶን የጃፓን ሩዝ ለምግብ ድጋፍ ፕሮግራም ይቀርባል።
ሁለተኛው ስምምነት ደግሞ የቡድን 7 አገራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ ከደረሰው ምጣኔ ሀብታዊ ተጽዕኖ እንዲያገግሙ ለማስቻል የተፈቀደው የዕዳ ክፍያ ማራዘሚያ ኢኒሼቲቭ የማስፈጸሚያ ስምምነት ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታዋ ያስሚን ወሃብረቢ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያና ጃፓን ወዳጅነት ከ1970ቹ ጀምሮ ጠንካራ እንደሆነ ገልጸው፤ በሁሉም የልማት መስኮች የጃፓን ድጋፍ ቀጣይነት ያለው ነው ብለዋል።
ጃፓን በሰው ኃይል ግንባታ፣ በችግር ጊዜ ደራሽ እገዛና ለፀረ-ኮቪድ መከላከል ጥረት ለምታደርገው ድጋፍም የኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና ይሰጣል ነው ያሉት።
የቡድን 7 አገራት የ2020 ዕዳ ክፍያ ማራዘሚያ ውሳኔን ተግባራዊ ለማድረግ የተደረገው ስምምነትም የጃፓን መንግሥትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የምግብ አቅርቦት የሰው ልጅ ደህንነት ቁልፍ ጉዳይ ነው ያሉት አምባሳደር ኢቶ፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ድርቅና ጎርፍ መሰል ችግሮችን ጋር የተያያዙ የምግብ ዋስትና ችግርን ለማቃለል ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ጃፓን ከአውሮፓዊያኑ 2015 ጀምሮ የሩዝ ምርት ትኩረት ከሚደረግባቸው ቁልፍ የግብርና ዘርፍ የድጋፍ መስኮች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
በእርዳታ የሚቀርበውን ሩዝ በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ በማዳረስ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ኢትዮጵያ ለምግብ ግዥ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ እንደሚያድን ገልጸዋል።
ጃፓን የኢትዮጵያዊያንን ኑሮ ለማሻሻል በተለያዩ የልማት ፕሮግራሞች በንቃት ስትሳተፍ መቆየቷን አውስተው፤ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር እንሰራለን ብለዋል።
በተለይም በመሰረተ ልማት፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በትምህርትና በጤና መስክ የነበራትን ፕሮጀክቶችን የመደገፍ ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
ጃፓን በተወሰነ መጠን ለኢትዮጵያ ብድር መስጠቷን አስታውሰው፤ ሁለተኛው ስምምነት የቡድን 7 አገራትን የዕዳ ክፍያ ማራዘሚያ ኢኒሼቲቭ ገቢራዊ ለማድረግ የጃፓን ፍላጎትና እምነት ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
ዛሬ የተደረጉት ስምምነቶች የሁለቱን አገራት መንግሥታትና ሕዝቦች ወዳጅነትና ትብብር ይበልጥ ለማጎልበት ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው አንስተዋል።