ቀጥታ፡

አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለመደምሰስ በሚካሄደው እንቅስቃሴ ለመሳተፍ የመንግሥትን ጥሪ እየተጠባበቅን ነው... የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 20/2013 (ኢዜአ) አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለመደምሰስ በሚካሄደው እንቅስቃሴ ለመሳተፍ የመንግሥትን ጥሪ እየተጠባበቁ መሆናቸውን በሻሸመኔ ከተማ የሚገኙ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ድጋፍና ልማት ማህበር አባላት አስታወቁ።

አባላቱ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በሀገር ላይ ክህደት የፈፀመውን ጁንታ ለማስወገድ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ሆነው ማንኛውንም ተልዕኮ ለመወጣት ዝግጁ ናቸው።

የማህበሩ ተወካይ ምክትል አሥር አለቃ ፈይሣ በዳኔ የማህበሩ አባላት ጁንታው የህወሓት ቡድን የመንግሥትን የተናጠል ተኩስ ማቆም አጋጣሚ ተጠቅሞ ወደ አጎራባች ክልሎች እያደረገ ያለው መስፋፋት እንዳስቆጣቸው ገልጸዋል።

አሸባሪውን ለመደምሰስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በመደገፍ በሀገራዊ ግዳጅ ላይ  ለመሳተፍ የመንግሥትን ጥሪ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወንበዴው ቡድን ሀገር ለማፍረስ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ሕጻናትን ጭምር ለጦርነት በመማገድ  እየፈጸመ ያለውን ወረራ አጥብቀው እንደሚቃወሙም  አስታውቀዋል።    

 ሌላኛው የማህበሩ አባል ሻምበል ካሣዬ ጉርሙ በበኩላቸው፤ በቀድሞ ጦር ሰራዊት ውስጥ በተለያዩ ክፍሎች በማገልገል የካበተ ልምድ እንዳላቸው አውስተው፤ ይህንን ልምዳቸውን በመጠቀም የሀገሪቱን አንድነት ለመናድ የሚቅበዘበዘውን ቡድን ለመደምሰስ  በሚካሄደው እንቅስቃሴ ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

"ባለኝ ወታደራዊ ዕውቀት በመጠቀም ሀገሬን  ካጋጠማት ችግር ለማውጣት በመዝመት  ለወጣቶች አርአያ መሆን እፈልጋለሁ" ብለዋል።

የራሱን ዕድሜ ለማርዘም የሚፍጨረጨረውን ጁንታ ዜጎች በአንድነት ተነስተው ድባቅ ለመምታት መነሳታቸው የተረዳ እንደማይመስላቸው  የተናገሩት ደግሞ ሌላው የቀድሞ የሠራዊቱ አባል ወታደር ግርማ ታረቀኝ ናቸው።

በዚህ ረገድ የቀድሞ ሰራዊት አባላት የመንግሥት ጥሪ ተቀብለው ለመንቀሳቀስ  መነሳታቸውን አስታውቀዋል።

የቀድሞ ሠራዊት አባል መቶ አለቃ ዓሊ ጃርሶ በበኩላቸው፤ "በጁንታው የተቃጣው  ኢትዮጵያን  የማፍረስ ዘመቻ እጅጉን ልባችን ደምቷል" ብለዋል።

በጦር ሜዳ በተደጋጋሚ የመቁሰል አደጋ እንደገጠማቸው ያወሱት ፤ መቶ አለቃ ዓሊ፣'' ዛሬም ለሀገሬ ክብር ስል ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ማንኛውንም መስዋዕትነት  ለመክፈል ዝግጁ ነኝ'' ሲሉ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያውያን በሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ  የተነሳባቸው የህወሓት የሽብር ቡድንን ለመደምሰስ ከየአቅጣጫው መነሳሳታቸውን በተለያዩ መንገዶች በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።

ወጣቶች የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል ላይ ሲሆኑ፤ ሕዝቡም በደጀንነት ተሰልፎ በገንዘብና ስንቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም