ቀጥታ፡

ወጣቶች የመከላከያ ሠራዊቱን ለመቀላቀል ያሳዩት ተነሳሽነት ታሪክ የማይረሳው ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 20 ቀን 2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ወጣቶች የመከላከያ ሠራዊቱ ለመቀላቀል ያሳዩት ተነሳሽነት የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚያኮራና ታሪክም የማይረሳው መሆኑን ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ ተናገሩ።

ምክትል ከንቲባዋን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች "ኢትዮጵያን ለማዳን እዝምታለሁ" በሚል የመከላከያ ሠራዊቱን የሚቀላቀሉ የመዲናዋን ወጣቶች ሸኝተዋል።

ወጣቶቹ ጀግናውን የመከላከያ ሠራዊት ለመቀላቀል ያሳዩት ተነሳሽነት ታሪክ የማይረሳውና የኢትዮጵያን ሕዝብ በእጅጉ የሚያኮራ ተግባር እንደሆነ ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል።

ለበርካታ ዓመታት ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ሲበድል ለቆየው አሸባሪው የህወሓት ቡድን በመደመር እሳቤና ይቅር ባይነት ለአገር እድገትና ሠላም እንዲሰራ አማራጭ ሲቀርብለት መቆየቱንም አስታውሰዋል።

ነገር ግን አሸባሪው ቡድን የቀረበለትን አማራጭ በመተው የመከላከያ ሠራዊቱን ከጀርባው በመውጋት ኢትዮጵያን ለማተራመስና ለማዳከም እየሰራ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ቡድኑ ያነገበውን አፍራሽ ተልዕኮ ለማፍረስና ከመከላከያ ሠሰራዊት ጎን ለመቆም የአዲስ አበባ ወጣቶች ያሳዩትን ተነሳሽነት ታሪክ ሲያወሳው እንደሚኖር ገልጸዋል።

'የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ አካልና ወገናችን ነው' ያሉት ወይዘሮ አዳነች ነገር ግን ማንም ቢሆን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚጥሩ አካላት ጋር ከተቀላቀለ 'አንታገሰውም' ብለዋል።

 አሸባሪ ቡድን በአውሮፓና በአሜሪካ ልጆቹን እያንደላቀቀና እያስተማረ  የክልሉን ወጣቶች ከሚያስፈጀው አካል የትግራይ ሕዝብ  ራሱን መነጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች ለሠራዊቱ ድጋፍ እንዲውል በአጭር ጊዜ የተሰበሰበውን 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ለመከላከያ ሚኒስቴር አስረክበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም