የዓለም ባንክ በከፍተኛ ትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ባንክ በከፍተኛ ትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር ተገለጸ
ሐምሌ 20 ቀን 2013 (ኢዜአ) የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርትና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ተመራ የከፍተኛ ስራ ሀላፊዎች ቡድን ከዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ኡስማን ዲዮን ከተመራው በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ጽ/ቤት ስራ ኃላፊዎች ቡድን ጋር ተወያይቷል፡፡
በዉይይቱም በዓለም ባንክ ድጋፍ እየተከናወነ የሚገኘው የምስራቅ አፍሪካ ክህሎት ሽግግርና ቀጠናዊ ትስስር ፕሮጀክት (EASTRIP) በኢትዮጵያ ከሚሰሩ ሰባት የቴክኒክና ሙያ ልህቀት ማዕከላት እና በአዲስ አበባ የሚገነባው የከፍተኛ ትምህርት የጥራት ማረጋገጫ ማዕከል ግንባታ ስራ ስለደረሰበት ደረጃ ገለጻ ቀርቧል፡፡
የሀገሪቱን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትን ተጠቃሚ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀክትን ስራ ለማስጀመር ስለተከናወኑ ተግባራትና አሁን ስለደረሰበት ደረጃ ማበራሪያ የተሰጠ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ከአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በበይነመረብ ተሳስረው በምርምርና መሰል ተግባራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተጀመረው ስራ ስላለበት ሁኔታ ተነስቷል።
ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር የዓለም ባንክ ቡድን ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርትና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና በተለይም በEASTRIP እያደረገ ስላለው ድጋፍ አድናቆትና ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ በጥራት እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ በነዚህና በሌሎችም አዳዲስ ፕሮጀክቶች የዓለም ባንክ ድጋፍ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ሚስተር ኡስማን ዲዮን የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በዓለም ባንክ ድጋፍ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በታቀደላቸው መሰረት እየተመሩ ያሉና አበረታች መሆናቸውንና የዓለም ባንክ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የከፍተኛ ትምህርት አቅርቦት፣ጥራትና አግባብነት ከማረጋገጥ አንፃር በአምስት አመት ውስጥ አምስት ሺ የፒኤች ዲ ምሩቃንን ለማፍራት የተዘረጋው የሀገር በቀል የሶስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር HCPP እና በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውና በቅርቡ “ወደ ዕውቀት መር ኢኮኖሚ” በሚል መሪ ቃል በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የከፍተኛ ትምህርት ምርምር፣ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን HEART የወደ ፊት ዓላማ በተለይም የአፍሪካ ኮንቬንሽን ሆኖ ለመቀጠል ስላለው ዕቅድ ማብራሪያ ቀርቧል።