የተተከሉ ችግኞችን በቋሚነት ለመንከባከብ የመሬት ይዞታ ካርታ ተረክበናል ---የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የተተከሉ ችግኞችን በቋሚነት ለመንከባከብ የመሬት ይዞታ ካርታ ተረክበናል ---የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን
አዳማ፤ ሐምሌ 19/2013 (ኢዜአ) ዘንድሮ የተተከሉ ችግኞችን በቋሚነት ለመንከባከብና ለሚፈለገው ጥቅም ለማዋል የመሬት ይዞታ ካርታ ተረክበናል ሲሉ የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ሃላፊ አቶ ጥላሁን ዋደራ ገለጹ።
የባለስልጣኑ አመራርና ሠራተኞች በምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ገላጣ በሆነ ሁለት ሄክተር መሬት ላይ የችግኝ ተከላ አካሄደዋል።
በዚህ ወቅት አቶ ጥላሁን እንደገለጹት፤ ባለስልጣኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ችግኝ ተክሏል።
ይሁንና የተተከለውን ችግኝ በባለቤትነት ከመንከባከብ አንፃር ክፍተቶች እንደነበሩ ጠቅሰው፤ "ዘንድሮ የተተከሉ ችግኞችን በቋሚነት ለመንከባከብና ለሚፈለገው ጥቅም ለማዋል ከወረዳው በባለስልጣኑ ስም የመሬት ይዞታ ካርታ ተረክበናል" ብለዋል።
ባለስልጣኑ በተረከበው መሬት ላይም የጠቅላይ ሚኒስትሩን "ኢትዮጵያን እናልብሳት" ጥሪ በመቀበል ዛሬ ከ2 ሺህ 500 በላይ ችግኝ መትከላቸውንና በቀጣይም ለመንከባከብ መወሰናቸውን ተናግረዋል።
በችግኝ ተከላው ላይ የተገኙት የባለስልጣኑ ሠራተኛ ወይዘሮ ድሪቤ ዱፌራ በበኩላቸው፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት በችግኝ ተከላው ቢሳተፉም በቋሚነት ችግኝ መንከባከብ ላይ ክፍተት እንደነበር አስታውሰዋል።
ዘንድሮ የተተክሉትን ችግኞች ተንከባክቦ በባለቤትነት ለማሳደግ ባለስልጣኑ ቋሚ ቦታ መረከቡ ጥሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
"የተረከብነውን መሬት ለደንና ለምግብነት በሚውሉ የችግኝ ዝርያዎች እንሸፍናለንም" ብለዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ተፈሪ መኮንን " ኢትዮጵያን እናልብሳት የጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጥሪ ተከትለን ዛሬ በተረከብነው ይዞታ ላይ ችግኝ ተክለናል" ብለዋል።
በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተሳተፉ አመራርና ሠራተኞቹ እያንዳንዱ ተቋም የተከላቸውን ችግኞች በሃላፊነትና ተጠያቂነት ተንከባክቦ ማሳደግ እንዳለበት ጠቁመዋል።