ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳው አሸባሪው ህወሃትን በአንድነት መታገል ያስፈልጋል - የፖለቲካ ፓርቲ አባላት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪው የህወሃት ቡድንን በአንድነት በመታገል አገርን ማዳን ያስፈልጋል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ገለጹ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጋር በስልክ ባደረገው ቃለ ምልልስ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት፤ አትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪውን የህወሃት ቡድን መታገልና አገር ማዳን ያስፈልጋል።  

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዶክተር በቃሉ አጥናፉ፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳው አሻባሪ የህወሓት ቡድንን ህዝቡ በአንድነት እንዲታገለው ማድረግ የፓርቲያቸው አቋምም እንደሆነ ጠቁመዋል።

የአሸባሪው የህወሓት ቡድንና አባሎቹ ከድርጊታቸው እስኪቆጠቡ ድረስ፤ "የተከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ አገርን መታደግ እንደሚገባ እናምናለን" ብለዋል።

በአንድነት በመሆን "አሸባሪዎችን ማጥፋት ይገባል" ያሉት ዶክተር በቃሉ፤ ይህ ካልሆነ የአገሪቷን ሰላም ማረጋገጥ እንደማይቻልም ተናግረዋል።

ስለዚህ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ከትግራይ ክልል ህዝብ በመነጠልና እርምጃ በመውሰድ የኢትዮጵያን ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አሸባሪውን የህወሃት ቡድን "ለመከላከል የሚወሰድ እርምጃ በምንም መልኩ ማንንም ተጠያቂ አያደረግም" ያሉት ዶክተር በቃሉ፤ አገርን ለማፍረስ የመጣን ሃይል በጋራ መመከት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።

አሸባሪው የሕወሃት ቡድን የሽብር ድርጊት ለአንድነት የማይበጅና የማይጠቅም መሆኑን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት እንዲቆም ጥሪ የማድረግን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጠውታል።

"ህዝቡ የአገርን አንድነት ለማፍረስ የሚመጣን አሸባሪ ቡድንና ስብስብ በምንም መልኩ መታገስ የለበትም ሊያወግዘውም፤ ሊታገለው ይገባል" ብለዋል።

የምዕራብ ሶማሌ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ሂርሲ ዶል በሰጡት አስተያየት፤ አሸባሪው ቡድኑ በየጊዜው በአገር ላይ እያደረሰ ያለውን ኪሳራ በተባበረ ክንድ መመከት እንደሚገባ ጠቁመዋል። 

ሁሉም ችግሩን ቆም ብሎ አስቦ ባለው አቅምና ጉልበት አገርን የመታደግ ስራውን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የእናት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰይፈስላሴ አያሌው በበኩላቸው፤ አሸባሪውን የህወሃት ቡድን መታገል ያስፈልጋል።

ፓርቲው በቅርቡ ባወጣው መግለጫ የአሸባሪው የህወሃት ቡድን በተደጋጋሚ አገር ወዳድ ሽማግሌዎች ያደረጉትን የማወያየትና የማቀራረብ ሂደት እንዳይሳካ ማድረጉን አስታውሰዋል።

እንደ አገር የፖለቲካ ፓርቲ እየተወሰደው ያለውን እርምጃ በተመለከተ በቅርቡ መግለጫ እንደሚያወጣም ነው የገለጹት። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም