ቀጥታ፡

የሀገርን ህልውና ለማስከበር ከጁንታው ጋር ለሚፋለመው መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ እናደርጋለን- የአሶሳ ነዋሪዎች

አሶሳ ሐምሌ 19 / 2013(ኢዜአ) የሀገርን ህልውና ለማስከበር ከህወሀት ጁንታ ጋር እየተፋለመ ካለው መከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ዛሬ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ ።
ሰልፈኞቹ ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ በመግለጽ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ጥቃትና ተጽዕኖን አውግዘዋል።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ መሳፍንት ዓለምነው ለኢዜአ እንደገለጹት  የምዕራባዊያን ተጽእኖ የኢትዮጵያን ሕዝብ በሉዓላዊነቱ ጉዳይ ከያዘው አቋም  አያስቀይረውም።

"በሀገሩ ጉዳይ የሚወስነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ የውጭ ሃይሎች አይደሉም " ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመሪው ጎን በመቆም በሀገሩ ህልውናና መጻኢ ዕድል ላይ እየወሰነ መሆኑን ተናግረዋል።

ህጻናትን፣ እናቶችንና አረጋውያንን አስገድዶ ወደ ጦርነት እየማገደ የሚገኘውን አሸባሪውን ህወሃት ለመመከት በገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ከሠራዊቱ ጎን ተሰልፈው የህይወት መስእዋትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል ፡፡

"ኢትዮጵያዊያን አንድ ከሆንን ከብረት የጠነከርን ነን"  ያሉት ደግሞ አቶ መንበረ አያሌው ናቸው፡፡

የውጭ ተጽዕኖ ቢበዛብንም አንገታችንን አያስደፋንም ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል።

"ህወሃት እያደረሰ ያለው ጥፋት ጊዜያዊና የምናልፈው ጉዳይ ነው" ያሉት አቶ መንበረ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን እንደሚሰለፉ አስታውቀዋል፡፡

ወይዘሮ ዘምዘም ሰይድ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው "የህወሃት የጥፋት ቡድን በወገን ላይ በሚያደርሰው ጉዳት አዝኛለሁ" ብለዋል፡፡

መከለከያ ሠራዊታት በሚያደርገው ተጋድሎ የሀገር ሠላም ሙሉ በሙሉ እስኪከበር  ድረስ በገንዘብ፣ በጉልበትም ሆነ በቁሳቁስ እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

"የሀገር መከላከያ ሠራዊት ማለት ለሀገር ህልውና የቆመ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስድ አካል ነው" ያሉት ደግሞ  አቶ ጃኩዚ ዑመር ናቸው።

''ሠራዊታችንን ለመደገፍ ሰልፍ መውጣቴ በእጅጉ አስደስቶኛል'' ብለዋል፡

"ከሀገር ህልውና በተቃራኒ የቆሙ አካላትን በምንም መልኩ መተባበር የለብንም" ያሉት አቶ ጃኩዚ  የኢትዮጵያ ሠላም እስኪረጋገጥ ለሠራዊቱ አስፈላጊውን ድጋፍ  እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡

የአሶሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ዑመር መሐመድ ኢትዮጵያ 6ኛውን አገራዊ ምርጫና የህዳሴ ግድብ  2ኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በማጠናቀቅ ማሸነፏን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ስኬት ጫና ሲያደርጉባት የነበሩ ሃይሎች ያልጠበቁትና ያስደነገጣቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ሠላም ሲኖር ሀገር ትኖራለች፤ እኛም እንኖራለን፤ ሕዝባችንም ከምርቱ ይጠቀማል፤ ከምዕራባዊያን ጫናም እንላቀቃለን "  ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም