ኢትዮጵያና ኤርትራ የጋራ የንግድ ቀጠና ሥርዓት መዘርጋት አለባቸው - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ኤርትራ የጋራ የንግድ ቀጠና ሥርዓት መዘርጋት አለባቸው - ምሁራን
አዲስ አበባ ነሀሴ 2/2010 በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የምጣኔ ሀብት ውህደትን ለማቀላጣፍ የሚያስችል የጋራ የንግድ ቀጣና ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ። በሁለቱ አገራት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ግንኙነቱን ለማጠናከር መንግሥት በምጣኔ ሀብት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ላይ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና እንደገለጹት ሁለቱ አገራት የሚያደርጉት የንግድ ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ መሆን አለበት። በአሁኑ ወቅት በአገራቱ ያለውን የንግድ አደረጃጀቶች በማጤን በድንበር አካባቢዎች የጋራ የጉምሩክ ሥርዓት የሚፈጠርበትን ሁኔታ ማመቻቻት እንደሚገባም ገልጸዋል። የጋራ የጉምሩክ ሥርዓቱ አገራቱ እርስ በርስ የሚለዋወጧቸውንና ከውጭ የሚያስገቧቸውን ዕቃዎች በተመለከተ የሚጣለውን ቀረጥ በጋራ ለመተመንና ለመጠቀም ያስችላል ብለዋል። እንዲህ ዓይነቱ የምጣኔ ሀብት አጋርነት ከረጅም ጊዜያት በኋላ ሁለቱ አገራት አንድ የመገበያያ ገንዘብ እንዲኖራቸው በር እንደሚከፍትላቸውም አቶ ክቡር ጠቁመዋል። እንደ አቶ ክቡር ገለጻ ኢትዮጵያና ኤርትራ አንድ የመገበያያ ገንዘብ እንዲኖራቸው ለማድረግ ሁለቱ አገራት የውጭ ምንዛሪ ተመናቸውን ተቀራራቢ ለማድረግ የጋራ ስምምነት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ኢትዮጵያና ኤርትራ የጋራ የንግድ ቀጣና ሲፈጥሩ የመጀመሪያዎች የዓለም አገራት እንዳልሆኑ የጠቆሙት አቶ ክቡር ከዚህ በፊት "ናፍታ"ን የተባለ የጋራ የንግድ ስምምነት በአሜሪካ፣ በካናዳና በሜክሲኮ የተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገው የንግድ ስምምነት ተጠቃሚ የሚያደርገው አገራቱን ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ያሉ አገራትንም ጭምር ሲሆን በቀጣናው ሰላም ላይ ቀጥተኛ ያልሆነ አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወትም አብራርተዋል። በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ረዳት ፕሮፌሰር ካሳ ተሻገር በበኩላቸው በኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ የኤርትራ አጋርነት ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት በሁለቱ አገራት መካከል የጋራ ነፃ የንግድ ቀጣና እና የጋራ የጉምሩክ ሥርዓት ለመዘርጋት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መሥራት እንዳለበትም ገልጸዋል። የጋራ የንግድ ቀጣና እና የጉምሩክ ሥርዓቱ የአገራቱን የንግድ ልውውጥ ከማጠናከር ባሻገር ከሌሎች አገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከርም ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል። ይህ ዓይነቱ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለኤርትራ ቅድሚያ ይሰጥ እንጂ ከቀጣናው አገራት ጋርም በተመሳሳይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ረዳት ፕሮፌሰሩ ጠቁመዋል። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት /ኢጋድ/ ድጋፍ በማድረግ በአውሮጳ ኅብረት አባል አገራት መካከል እንዳለው አጋርነት በቀጣናው መፈጠር አለበት ብለዋል። ኢትዮጵያና ኤርትራ በሚያዋስኗቸው ድንበር ምክንያት በፈጠሩት ውዝግብ ለሁለት አስርተ ዓመታት የተቋረጠው ግንኙነት በቅርቡ በሁለቱ አገራት መሪዎች አማካይነት ሰላም ተፈጥሯል።