ቀጥታ፡

የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት 12ኛ መደበኛ ጉባኤ ተጀመረ

ጋምቤላ፤ ሐምሌ 19/2013(ኢዜአ) የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ስድስተኛው የስራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በጋምቤላ ከተማ ተጀመረ።

የክልሉ ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ አቶ ጁል ናንጋል በጉባኤው መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት እንደተናገሩት፤ እንደ ሀገር ያገጠመውንን ፈተና ተባብሮ  በማለፍ የተጀመረውን የለውጥና የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ሁሉም ጠንክሮ መስራት ይገባል።

አሸባሪው የህወሓት ጁንታ የተጀመረውን የለውጥና የብልጽግና ጉዞ ለማስናከል ከውስጥና ውጭ ኃይሎች ጋር ተናቦ እየሰራ ቢሆንም ጫናዎቹን በመቋቋም ስኬት የተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትና ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት መጠናቀቃቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የአሸባሪ ቡድኑን ሀገር የማፍረስ ሴራ በማክሸፈ ስኬቶችን ለማስቀጠል በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ህዝቡን በማስተባበር ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ጉባኤው በሚኖረው የሶስት ቀናት ቆይታ የክልሉን የ2013 በጀት ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር፣ የኦዲትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት የስራ ክንውን ሪፖርቶችን መርምሮ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

እንዲሁም የተያዘው በጀት ዓመት የልማትና መልካም አስተዳደር እቅድ፣ የማስፈፀሚያ በጀትና የተለያየዩ አዋጆችን በጉባኤው እንደሚያጸድቅ መገለጹንከስፍራው ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም