ቀጥታ፡

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሴቶች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ስንቅ አዘጋጁ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሴቶች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ስንቅ አዘጋጅተዋል።

ለአገር መከላከያ ሠራዊት እየተደረገ ያለው ድጋፍና የስንቅ ዝግጅት በአገራዊ አብሮነትና የአንድነት ስሜት እንደቀጠለ ነው።

ዛሬ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሴቶች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ስንቅ አዘጋጅተዋል።

የክፍለ ከተማው ሥራ አስፈጻሚ አቶ ይታያል ደጀኔ፤ የክፍለ ከተማው ሴቶች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ደጀንነታቸውን ለማሳየት ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

አጥፊውን ኃይል በአንድነት ሆኖ ማስቆም ካልተቻለ ለአገሪቷ ልማትና ሠላም ፀር ስለሚሆን መከላከያ ሠራዊቱን ባለን አቅም መደገፍና ደጀን መሆን አለብን ብለዋል።

በስንቅ ዝግጅቱ የተሳተፉት ሴቶችም አብሮነታቸውን በማጠናከር ከስንቅ ዝግጅቱ በተጨማሪ ግንባር ድረስ ሄደው ሠራዊቱን ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።

የአገር መከላከያ ሠራዊት የምድር ኃይል መምሪያ የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ ኮሎኔል ሁሉ አገርሽ ደረሰ በበኩላቸው ሴቶቹ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ደጀንነት ለማሳየት ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።

ድጋፉ ለሠራዊቱ ከፍተኛ ሞራል እንደሚሆነው ገልጸው፤ በቀጣይም የአካባቢያቸውን ሰላም እየጠበቁ ለአገር መከላከያ ሠራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም