የምዕራብ አርሲና የሻሸመኔ ከተማ ህዝብ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት አጋርነቱን እንደሚያጠናክር ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የምዕራብ አርሲና የሻሸመኔ ከተማ ህዝብ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት አጋርነቱን እንደሚያጠናክር ገለጸ
ሐዋሳ፣ሐምሌ 18/2013 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ አርሲ ዞንና የሻሸመኔ ከተማ ህዝብ በግዳጅ ቀጠና ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ዛሬ ባካሄዱት ህዝባዊ ሰልፍ አስታወቁ።
ሰልፈኞቹ አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን የሚያወግዙ መፈክሮችን በማንገብ ነው የድጋፍ ሰልፍ ያደረጉት።
ካሰሟቸው መፈክሮች መካከልም በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ሴራ ኢትዮጵያ አትፈርስም፣ የአሸባሪውን የህወሃት ትንኮሳ እናከሽፋለን፣ እኛ የጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ደጀን ነን፣ የትግራይ ህዝብ ወዳጃችን ነው አሸባሪው ህወሓት የኢትዮጵያ ጠላት ስለሆነ በተባበረ ክንዳችን ግብዓተ መሬቱን እንፈጽማለን ብለዋል።
የጦር መሣሪያ ከትግራይ ህፃናት ትከሻ ላይ እንዲወርድ የዓለም መንግስታት የቡድኑን ህገ-ወጥ ተግባር ሊያወግዝ ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል።
ሰልፈኞቹ ለመከላከያ ሰራዊትና ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርጉም በድምጻቸው አረጋግጠዋል።
ከድጋፍ ሰልፉ ተካፋዮች መካከል የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ ሸምሲያ አልይ ለኢዜአ በሰጠችው አስተያየት “የጁንታውን የጥፋት እንቅስቃሴ ለመቃወምና ለሀገር መከላከያና ለህዳሴ ግድብ ያለኝን አጋርነት ለመግለጽ በሰልፉ ተገኝቻለሁ” ብላለች።
“የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር በግዳጅ ላይ ለሚገኘው ሰራዊት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማድረግ በሚችለው አቅም ሁሉ እገዛ ማድረግ ስላለበት በዚህ ረገድ የሚጠበቅብኝን እወጣለሁ” ብላለች።
ሌላኛው የሰልፉ ተሳታፊና የሻላ ወረዳ ነዋሪ ጫላ አብደላ በበኩሉ ተሳትፎዬ በቁሳቁስና በድጋፍ ሰልፍ ብቻ የሚገደብ ሳይሆን አገር አፍራሾች እስከሚከስሙ ግንባር ድረስ በዘመቻ ለመሳተፍ በመዘጋጀት ነው ብሏል።
አቶ ቁፋ ጎቤ በበኩላቸው “ሰላም ሲኖር ነው በሀገር መኖር የሚቻለው” በማለት ከውጭና ከውሰጥ ሆነው ሀገራችንን ለማፍረስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመቃወም መሳተፋቸውን ተናግረዋል።
በተለይ የዞኑና የከተማው ህዝብ ከዚህ የድጋፍ ሰልፍ በተጨማሪ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰንጋና ስንቅ በማዘጋጀት አጋርነታቸውን እየገለጹ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጉታ ላቾሮ የሀገራችን ሉአላዊነት ተከብሮ የሚቀጥለው ልክ እንዳዛሬው በአንድነት ስንቆም ሰለሆነ ህዝቡ ለሰራዊቱ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከንቲባው በድጋፍ ሰልፉ በመገኘት ለሃገር መከላከያ ሰራዊት አጋርነታቸውን ለገለጹ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።