አሸባሪው ህወሓት ለሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርና ቁሜለታለሁ ለሚለው ለትግራይ ህዝብ ደንታ የለውም... የትግራይ ተወላጆች - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት ለሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርና ቁሜለታለሁ ለሚለው ለትግራይ ህዝብ ደንታ የለውም... የትግራይ ተወላጆች
ሰመራ፣ ሀምሌ 18/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርና ቁሜለታለሁ ለሚለው ለትግራይ ህዝብ ደንታ እንደሌለው በጦርነቱ ያሰለፋቸው ሕጻናት በቂ ማሳያ ናቸው ሲሉ በአፋር ክልል የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ገለጹ።
ዛሬ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለማውገዝና ለመከላከያ ሠራዊት አጋርነትን ለማሳየት ያለመ ህዝባዊ ሰልፍ በሠመራ-ሎግያ፣ አይሳኢታና አበአላ ከተሞች ተካሂዷል።
በሠመራ-ሎግያ ከተማ ከተካሄው በዚህ ሰልፍ በከተማው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ተሳትፈውበታል።
ከተሳታፊዎቹ መካከል የሠመራ ከተማ ነዋሪ አቶ ሁሪ አብርሃ እንዳሉት ከጦርነት የሚገኝ አንዳችም ጥቅም አለመኖሩን መንግስት ተገንዝቦ ተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፉ ሽንፈት ሳይሆን ሃላፊነት ከሚሰማው አካል የሚጠበቅ የሰከነ ውሳኔ ነው።
ጁንታውና ደጋፊዎቹ እንደሚሉት መንግስት የትግራይ ህዝብ ጠላት ሳይሆን ባሳለፈው ውሳኔ ለትግራይ ህዝብ ያለውን ክብር በተጨባጭ አሳይቷል ነው ያሉት።
በተቃራኒው የህወሓት የጥፋት ቡድን ሆን ብሎ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየፈጸመ ያለው ትንኮሳና እየጎሰመ ያለው የጦርነት ነጋሪት ሃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን ይገልጻሉ።
ጁንታው በዚህ የጥፋት ተግባሩ በተለያዩ የሀገራቱ አካባቢዎች የእለት ኑሮውን ጥሮ ግሮ ለማሸነፍ የሚጥረውን ትግራዋይ ህይወት አደጋ ውስጥ ከመክተት ባለፈ ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የነበረውን አብሮነት ጥላሸት እየቀባው መሆኑን ነዋሪው ተናግረዋል።
በተጨማሪም የትግራይ ሕጻናትን ጨምሮ ያለምንም ርህራሄ ለጦርነት መማገዱ ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን ይቅርና ቆሜለታለሁ ለሚለው የትግራይ ህዝብ እንኳ ደንታ እንደሌለው ማሳያ መሆኑን ነው የገለጹት።
የሎግያ ከተማ ነዋሪ አቶ ሃይለስላሴ ገብሩ በበኩላቸው ህወሓት ከአመሰራረቱ ጀምሮ ንጹሀንን በመግደልና በማፈን ዕድሜውን ሲያራዝም የቆየ እኩይ ድርጅት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም እሳቸውን ጨምሮ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ለአገዛዙ ካልተመቸ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ቤተሰቡን በግፋ እንዲያጣ ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በቅርቡም መቀሌ የነበረው ትንሽ ወንድማቸው የብልጽግና ፓርቲን ትደግፍለህ ተብሎ በቡድኑ መታሰሩን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
"መንግስት በአሸባሪው ጁንታ ላይ በወሰደው እርምጃ ዳግም መነሳት በማይችልበት ደረጃ አቅሙ ቢሽመደመድም አሁንም በተስፋ-መቁረጥ ስሜት ሌላውን ይዞ ለመሞት እየተውተረተረ ይገኛል፤ ይሄም ዓላማው አይሳካም" ብለዋል።
የጥፋት ቡድኑ በህዝቦች የተባበረ ክንድ ካልተወገደ በስተቀር ለሌሎች አጎራባች ክልል ነዋሪዎች እንደማይተኛም አቶ ሃይለስላሴ ገልጸዋል።
ለዚህም የትግራይ ህጻናትና ሴቶችን አስገድዶ ወደጦርነት መማገዱ ጥሩ ማሳያ ከመሆን ባለፈ ታሪክ ይቅር የማይለው ግፍ መሆኑንም ነው ያመላከቱት።
በአፋር ክልል ከ40 ዓመት በላይ ሀብት አፍርተውና ቤተሰብ መስርተው እንደኖሩ የገለጹት ደግሞ አቶ ሃይላይ ሀጎሶ የተባሉ ሌላው የሎግያ ከተማ ነዋሪ ናቸው።
በነዚህ ዓመታት ከወንድም የአፋር ህዝብም ሆነ ከሌላ ብሔር ተወላጆች ጋር በክፉም ሆነ በደጉ በመደጋገፍ አብረው በሰላም መኖራቸውን ተናግረዋል።
"ይሁንና በሽብር ተግባር የተሰማራው ህወሓት ከአጎራባች ክልሎች ጋር እየፈጠረ ባለው ትንኮሳና የጦርነት አዋጅ ከማንም በላይ የትግራይ ህዝብ ተቆጥሮ ለማያልቅ መከራ እየዳረገው ነው" ብለዋል።
በመሆኑም በተለይ የትግራይ ህዝብ ዝምታውን ሰብሮ የተጫነበትን አፈና ፈንቅሎ በመውጣት የጥፋት ቡድኑን በቃ ሊለው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።