በአማራ ክልል ከተሞቹ የአሸባሪውን ህወሓት ድርጊት የሚያወግዙና የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፉ ሰልፎች ተካሄዱ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከተሞቹ የአሸባሪውን ህወሓት ድርጊት የሚያወግዙና የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፉ ሰልፎች ተካሄዱ
እንጅባራ፣ መተማ፣ ሐምሌ 18/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል እንጅባራና ምድረገነት ከተሞች የአሸባሪውን ህወሓት ድርጊት የሚያወግዙና የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፉ ሰላማዊ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው።
በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ ዞን እንጅባራ ከተማ እና ምድረገነት ከተማ የአሸባሪውን ህወሓት ድርጊት የሚያወግዙና የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፉ ሰላማዊ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው።
በአዊ ብሔረሰብ ዞን እንጅባራ ከተማ በተካሄደ ሰልፍ ላይ ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
በዞኑ ከሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከወጣቶች፣ ከመንግስት ሠራተኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የተለያዩ መፈክሮችንና መልክቶችን አሰምተዋል።
በሰልፉ ላይ ከተሰሙ መፈክሮች መካከል "በህወሓት የጥፋት ቡድን ላይ የሚወሰደውን እርምጃ እንደግፋለን፣ የኢትዮጵያዊያን መተባበር የአንድነታችን ሚስጥር ነው፣ ለአማራ ልዩ ኃይልና ለመከላከያ ሠራዊት ክብር እንቆማለን፣ ህወሓት ህጻናትን ለጦርነት እየማገደ ያለውን ድርጊት እናወግዛለን" የሚሉና የመሳሰሉት ይገኙበታል።
በተመሳሳይ ዜና በምዕራብ ጎንደር ዞን ምድረገነት ከተማ የሃገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ እንዲሁም የክልሎች የጸጥታ አካለትን የሚደግፍ ህዝባዊ ሰልፍ እየተደረገ ነው።
የድጋፉ ተሳታፊዎች እንዳሉት ሀገርን ከጥፋት ለማዳን መስዋዕትነትን ለሚከፍሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ከሃብት ድጋፍ በተጨማሪ ከጎናቸው ለመቆም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ከፍያለው አየነው እንደገለጸው አሁን እየተደረገ ያለው ዘመቻ ሀገርን የማዳንና አንድነትን የሚያጸና በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
በህወሓት የሽብር ቡድን ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ ዋጋ እየከፈሉ ቢሆንም የውጭ ጣልቃ ገብነትና ጫና ተጨማሪ ፈተና መሆናቸውን ተናግሯል።
የህወሓት የሽብር ድርጊትን ለመመከት አሁንም ህዝቡ በአንድ መቆሙን የገለጹት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪና የሰልፉ አስተባባሪ አቶ አዳነ ጥጋቡ ናቸው።
የሽብር ቡድኑ እየፈጸማቸው ባሉ እኩይ ተግባራት በተለይ ወጣትና ህፃናት ላይ ከፍተኛ ጉዳትና እንግልት እየደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።
ለሰብዓዊነት እንጨነቃለን የሚሉ የውጭ ሀገራት የሽብር ቡድኑን ተግባር ማውገዝ ቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።
"የከተማው ወጣቶች እንደአባቶቻቸው በሀገራቸው ጉዳይ አይደራደሩም" ያሉት አቶ አዳነ፣ ሀገርን ለማስቀጠል አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሌኛዋ የሰልፉ ተሳታፊ ወጣት እንይሽ መከተ በበኩሏ ከሽብር ቡድኑ ጋር ለሚፋለሙ ወገኖች ደጀን በመሆን የሀገሪቱን አንድነት ለማስቀጠል እንደምትሰራ ተናግራለች።
በሰልፉ ላይ "ከአባቶቻችን የተረክብናትን ሃገር ለልጆቻችን እናወርሳለን፣ ሽብርተኛን የሚታገል ሃገር ከኢተዮጵያ ጎን ሊቆም ይገባል፣ ህልውናችን በተባበረ ክንድ እናስከብራለን" የሚሉትና ሌሎችም መፈክሮች ተደምጠዋል።