አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለመበታተን የሸረበውን ሴራ በአንድነት በመቆም በጋራ መክቶ መቀልበስ ይገባል - የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለመበታተን የሸረበውን ሴራ በአንድነት በመቆም በጋራ መክቶ መቀልበስ ይገባል - የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት
ሀምሌ 18/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለመበታተን የሸረበውን ሴራ በአንድነት በመቆም በጋራ መመከት እንደሚገባ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ተናገሩ።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ለኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የድጋፍ ሰልፍ ዛሬ በመስቀል አደባባይ አካሂደዋል።
በዚህ ሰልፍ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የቀድሞ የሠራዊቱ አባላት እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአገርን ክብርና አንድነት ለመጠበቅ የህይወት መስዋዕትነት ጭምር እየከፈለ ይገኛል።
አሸባሪው ህወሓት "ለአገርና ህዝብ የሰሩ የቀድሞ ሠራዊት አባላትን "የደርግ ወታደር" በሚል ስያሜ በመስጠት ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈል እንዲመቸው ነበር" ያሉት አባላቱ፤ አሁን ደግሞ ለመከላከያ ሠራዊት ሌላ ስያሜ በመስጠት አንድነቱ እንዲላላ የማያደርገው ጥረት፣ የማሰራው ሴራ እንደሌለና ይህም መለያ ባህረው እንደሆነ አብራርተዋል።
የቀድሞውም ሆነ የአሁኑ መከላከያ ሠራዊት አባላት ለአገር አንድነትና ዳር ድንበር መከበር መስዋዕትነት የከፈሉ መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህ ፀረ ህዝብ የሆነ የሽብር ቡድን ኢትዮጵያን ለመበታተን በሚሸርበው ሴራ የሠራዊቱን ስም ማጠልሸት አንዱ መገለጫው መሆኑን ተናግረዋል።
አሸባሪው ህወሓት ስልጣን ላይ በነበረ ጊዜ የቀድሞ ሠራዊት አባላትን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውጪ አድርጎ እንደበተናቸው ያስታወሱት አባላቱ፤ ዳግም የዚህ ዓይነቱን እኩይ ተግባር ለመፈጸም እድልፈንታ እንደማይሰጠው ተናግረዋል።
ይህ ቡድን ገና ከጅምሩ የኢትዮጵያዊነት ስሜት የሌለውና የውጪ ተላላኪ መሆኑን ጠቁመው፤ እነርሱ ከአባቶች የተረከቡትን ነፃ አገር በከፈሉት ደም ነፃነቷን እንዳስጠበቁ ሁሉ ዛሬም ኢትዮጵያን ለማዳን ነፍሳቸውን ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የመቶ አለቃ ተፈራ አቡኑ፤ የሻምበል ተሾመ ከበደ እና የመቶ አለቃ በቀለ በላይ ይሄንን ነው የሚናገሩት።
አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለመበታተን የሸረበውን ሴራ በአንድነት በመቆም በጋራ መመከትና መቀልበስ እንደሚገባ ገልፀው፤ የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ በማንኛውም ግዳጅ ከመከለከያ ሠራዊቱ ጎን እንደሚሰለፉ አረጋግጠዋል።
የህወሓት ሽብር ቡድን በ1981 ዓ.ም በአላማጣ አካባቢ በተደረገው ጦርነት "ቤተክርስቲያንን ምሽግ አድርጎ ይዋጋ ነበር" የሚሉት የአስር አለቃ አሸናፊ በቀለ፤ ዛሬም ለሰብዓዊነት፣ ለሕዝቦች እምነትና ሃይማኖት ክብር የሌለው እኩይ ቡድን መሆኑን በተግባር ማሳየቱን ጠቁመዋል።
ይህ ቡድን ዛሬም እንደ ከዚህ ቀደሙ ህፃናትን፣ አዛውንቶችን ነፍሰጡሮችን ለእኩይ አላማው እየተጠቀመ መሆኑን ገልፀው፤ ህፃናትን እና አዛውንትን በጦርነት ማሳተፉ መሸነፉን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና ልማት ማህበር የበላይ ጠባቂ ብርጋዴር ጄነራል ዋሲሁን ንጋቱ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህወሓት ሰላም ወዳዱን የትግራይ ህዝብ የማይወክል መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ የሽብር ቡድን በምንም ዓይነት ሁኔታ ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይችል አብራርተዋል።