የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ለህልውና ዘመቻው የክተት ጥሪ አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ለህልውና ዘመቻው የክተት ጥሪ አስተላለፉ
ባህር ዳር፣ ሃምሌ 18/ 2013 (ኢዜአ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር የመንግስትና የግል መሳሪያ የታጠቀና የመዋጋት አቅም ያለው ሁሉ በህልውና ዘመቻው እንዲሳተፉ የክተት ጥሪ አስተላለፉ።
የክተት ጥሪው የተላለፈው የአማራ ህዝብን በማጥፋት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሞት ሽረት እያደረገ ያለውን አሸባሪው የህውሃት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ መሆኑ ተመላክቷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አገኘሁ ተሻገር ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት አሸባሪው ህወሃት በራያና በጠለምት ግንባር መጠነ ሰፊ ወረራ ለማድረግ የሞት ሽረት ትግል እያደረገ ይገኛል።
"የተከፈተብንን ወረራ ለመመከት የክልሉ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ከመከላከያ ሃይሉ ጎን በመሰለፍ ከአሸባሪው ጁንታ የሚላከውን ሃይል በመደምሰስ በህልውና ትግሉ አኩሪ ተጋድሎ እያደረጉ ይገኛሉ" ብለዋል በመግለጨቸው።
"በግንባሮቹ የሚላከው የአሸባሪው ሃይል የሞት፣ የመቁሰልና የመማረክ ኪሳራ ቢደርስበትም ከ12 - 65 ዓመት እድሜ የሚገኙ ህጻናትንና አዛውንቶችን ሳይቀር በገፍ እያሰለፈና እየማገደ ይገኛል" ብለዋል።
"ጁንታው በሞት ሽረት ትግል የሚያካሄደው ወረራ ዓላማው የአማራን ህዝብ በማዋረድ ኢትዮጵያን ለመበታተን መሆኑን ሁሉም ህዝብ ሊገነዘበው ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል።
ጁንታው የትግራይን ወጣት፣ ሴትና አዛውንት በላይ በላዩ በመጨመር በተራዘመ ጦርነት ያሰበውን ኢትዮጵያን የማፍረስ ግብ ለማሳካት እየሰራ መሆኑን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊያውቀው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ህዝብም አሸባሪው ጁንታ እያለ ምንም አይነት እረፍት የማያገኝ መሆኑን በመገንዘብ ለተላለፈው የህልውና ክተት ጥሪ ተሳታፊ እንዲሆን አሳስበዋል።
"በህልውና ጥሪው የመንግስትና የግል መሳሪያ ያለው ማንኛውም ግለሰብና የመዋጋት አቅም ያለው ወጣት ከነገ ጀምሮ በወረዳ ማዕከላት በመቅረብ ሪፖርት ማድረግ እንዳለበት" አስገንዝበዋል።
"ጸረ አማራና ጸረ ኢትዮጵያ የሆነውን አሸባሪ ቡድን ህዝቡን እየላከ ከማስጨረስ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለው አይተናል" ብለዋል።
"አሸባሪው ቡድን በአፋር ክልል ላይ ተመሳሳይ ወረራ በመፈጸም ጸረ ኢትዮጵያ መሆኑን አስመስክሯል" ያሉት አቶ አገኘሁ ቡድኑ በተባበረ ክንድ መጥፋት እንዳለበት አመልክተዋል።
"የትግራይ እናቶች ልጆቻችን የት ገቡ ብለው መጠየቃቸው ስለማይቀር ቡድኑ ቀድሞ ወደ ጦርነት የላከውን ህዝብ ወደ ኋላ ከመመለስ ይልቅ በእሳት መማገድን መርጧል "ብለዋል።
"አሸባሪውን ቡድን ማጥፋት የሚቻለው በመጣበት ስልት ምላሽ መስጠት ሲቻል መሆኑን በመገንዘብ የክልሉ ህዝብ ለክተት ጥሪው አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የአድዋን ድል መድገም አለበት" ሲሉ አስገንዝበዋል።
እስካሁን በተደረገው የህልውና ትግል መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በግንባር በመሰለፍና ድጋፍ በማድረግ ያሳየው ተነሳሽነት ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው የማይደራደሩ መሆናቸውን ያሳየ ተግባር በመሆኑ አመስግነዋል።
በተለየም የኦሮምያ ክልል ህዝብና መንግስት ግንባር ላይ ለተሰለፈው ሰራዊት ቀለብ የሚሆን ሰንጋ ጨምሮ የበግና የፍየል በድጋፍ በማቅረቡ አመስግነዋል።
መላ የክልሉ ህዝብም በማህበራዊ ድህረ ገጾች የሚዘዋወሩ ያልተረጋገጡ ወሬዎችን ከመስማት በመቆጠብ መረጃን ከትክክለኛው አካል መጠባበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።