ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ በማንኛውም ግዳጅ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እንሰለፋለን- የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት

ሀምሌ 18/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ በማንኛውም ግዳጅ ከመከለከያ ሰራዊቱ ጎን እንደሚሰለፉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት ተናገሩ።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና ልማት ማህበር አባላት ለኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የድጋፍ ሰልፍ በመሰቀል አደባባይ አድርገዋል።

በድጋፍ ሰልፉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና ልማት ማህበር የበላይ ጠባቂ ብርጋዴር ጄነራል ዋሲሁን ንጋቱ፣ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ፣ የመከላከያ ሰራዊት ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮረኔል ጌትነት አዳነ ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ብርጋዴር ጄነራል ዋሲሁን ንጋቱ እንዳሉት፤ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ነው።

"ኢትዮጵያ ሳይትሆን የህወሃት አሸባሪ ቡድን እንደሚፈርስ ማረጋገጥ አለብን" ያሉት ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን፤ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ በማንኛውም ግዳጅ ከመከላከያ ጎን እንደሚሰለፉ ተናግረዋል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳው አሸባሪው ህወሐትን  ለመመከት የሚደረገውን ጥረት ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮረኔል ጌትነት አዳነ፤ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር አስከብሮ ለትውልድ ያስረከበ መሆኑን ተናግረዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያን ለመከፋፈል እንዲመቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊትን "የደርግ ሰራዊት" በማለት በደል ሲያደርስበት መቆየቱን አስታውሰዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት ለመከላከያ ሰራዊቱ ላሳዩት ድጋፍና የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ ላሳዩት ዝግጁነት ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም