ቀጥታ፡

የሶስትዮሽ ስምምነቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስከበረ ነው- የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2010 በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በተካሄደው የሚኒስትሮች ስብሰባ የተደረሱ ስምምነቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስከበሩ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ለአንድ ዓመት ከሁለት ወራት ያህል በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የውጭ ጉዳይ፣ የውሃ ሀብት ሚኒስትሮች እንዲሁም በሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ሲደረግ የነበረው እልህ አስጨራሽ ውይይትና ድርድር ትናንት ሌሊት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከሱዳንና ግብፅ ጋር ድርድር ሲካሄድባቸውና ስምምነት ላይ ሳይደርሱባቸው የቆዩ የተለያዩ ጉዳዮች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ስምምነት ተደርሶባቸዋል። እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በተካሄደው የተሟሟቀ ክርክር ከግድቡ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ፣ ራሱን የቻለ ሳይንሳዊ ጥናት የሚያካሂድ ብሔራዊ ቡድንና   የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ፈንድ ከማቋቋም ጋር በተያያዙ ጉዳዮች  ዙሪያ ከመግባባት ላይ ተደርሷል። ከዚህ በፊት ግብጽ ልዩነቶች  በሶስተኛ ወገን አደራዳሪነት እንዲፈቱ  የነበራትን አቋም በመተው በምትኩ በግድቡ አሞላልና የውሃ አለቃቀቅ ላይ ራሱን የቻለ ሳይንሳዊ ጥናት ለማካሄድ ከሶስቱ አገሮች ከእያንዳንዳቸው አምስት አባላት የሚወከሉበት ቡድን እንዲቋቋም  ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ አማካሪው ባቀረበው የጥናት ማስጀመሪያ ሪፖርት ላይ የአገሮቹ  የማብራሪያ ጥያቄዎችና አስተያየቶች  በሶስትዮሽ ብሄራዊ የቴክኒክ ኮሚቴው ተደራጅተው ለአማካሪው ከቀረቡ በኋላ አማካሪው በሚሰጠው መልስ ላይ በቀጣይ ውይይት ማድረግ ሁለተኛው ስምምነት የተደረገበት ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ ግብጽ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆን ስታንጸባርቅ የነበረውን አቋሟን ትታ ወደ ስምምነቱ ተመልሳለች። የአገሮቹ መሪዎች ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜ በየተራ በመዲናቸው እንዲካሄድ ሚኒስትሮቹ ከመግባባት ላይ ደርሰዋል። የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ፈንድን ማቋቋም እንዲቻል ከሶስቱ አገሮች የሚመለከታቸው የውሃ ኃላፊዎች ግንቦት 26 እና 27 ቀን 2010 ዓ.ም በካይሮ ተገናኝተው የሚያቀርቡት  ማቋቋሚያ በመሪዎች ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በእንጥልጥል ላይ በነበሩ ጉዳዮች ከመግባባት መደረሱን ገልጸዋል። ሚኒስትሩ ስብሰባው በስኬት በመጠናቀቁ መደሰታቸውን ገልፀው፣ መግባባት ላይ የተደረሰባቸው ጉዳዮች የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን እንደሚያጠናክሩት ተናግረዋል። መግባባት ላይ እንዲደረስ ኢትዮጵያ ላደረገችው ጥረት ያመሰገኑት የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ውይይቱ የተካሄደበት መንፈስ ግልፅነትና ወንድማማችነት የተሞላበት እንደሆነ ገልጸዋል። የሱዳን ውሃ ሚኒስትር ሙታዝ ሙሳ ድርድሩ  ያለ ማንም ሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት  የጋራ ጉዳዮችን መፍታት ማስቻሉን መናገራቸውም በመግለጫው ተመልክቷል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም