ቀጥታ፡

በህገ-ወጥ መንገድ 51 ሰዎችን ወደ ሱዳን ሊያሻግር የሞከረው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

መተማ፣ ሐምሌ 17/2013( ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ 51 ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ ከሃገር ለማስወጣት ሲሞክር እጅ ከፍንጅ የተያዘ ግለሰብ በ11 ዓመት ፅኑ እስራትና በገንዘብ መቀጣቱን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የፍርድ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አበበ ማስሬ ለኢዜአ እንዳሉት ተከሳሹ ካልተያዘ ግብረ አበሩ ጋር በመሆን በተሽከርካሪ ደብቀው 51 ሰዎችን ወደ ሱዳን ለማሻገር ሲሞክር በቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ በህግ ሲታይ ቆይቷል።

የጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆነው ሰለሞን ጥጋቤ የተባለው ተከሳሽ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎ የመጡ ግለሰቦችን ከደላሎች በመቀበል ወደ ሱዳን ሊያሻግር ሲል ሃምሌ 2 /2013 ዓ/ም ገንዳ ውሃ ከተማ መያዙን አመልክተዋል። 

ኮድ 3 አ.አ A32469 በሆነ የጭነት ኤፍ ኤስ አር አይሱዙ ሰዎችን ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ በሸራ በመሸፈን ከሃገር ሊያስወጣ ሲሞክር በመያዙ በዞኑ አቃቢ ህግ ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ ሲመረመር መቆየቱን አስታውሰዋል።

በተደረገው ምርመራም ተከሳሹ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር1178/2012 አንቀፅ 8/3 ተላልፎ መገኘቱን ተናግረዋል።

ግለሰቡ የተመሰረተበትን ክስ እንዲከላከልና ማስተባበል እንዲችል እድል ቢሰጠውም መከላከያ ምስክር እንደሌለው ለፍርድ ቤቱ ማሳወቁን ገልፀዋል።

በመሆኑም አቃቢ ህግ የቀረበበትን የሰነድና የሰው ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻሉ በ16/2013 ዓ/ም በዋለው ችሎች ጥፋተኛ መሆኑ በመረጋገጡ 11 ዓመት ጽፅ እስራትና በ5 ሺህ ብር መቀጣቱን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በወቅቱ እስከ 25 ሺህ ብር ድረስ ለደላሎች የከፈሉ ከወላይታ ሶዶና ከሌሎችም አካባቢዎች የመጡ የዚህ ህገ-ወጥ ስደት ተሳታፊዎችን ጭምር በማናገር መዘገቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም