ቀጥታ፡

ሰራዊቱ ለሃገር ሉአላዊነት መጠበቅ ማንኛውንም መስዋዕትነት ይከፍላል - ሌተናል ጄነራል አስራት ዴኔሮ

ሃረር፤ ሐምሌ 17/2013 (ኢዜአ) መከላከያ ሰራዊት የሃገራችንን ሉአላዊነት ከውስጥና ከውጭ ጠላት በመጠበቅ የተጠናከረ አንድነቷን ለማስቀጠል ማንኛውንም መስዋዕትነት ይከፍላል ሲሉ በኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስቴር የምድር ኃይል ጠቅላይ መመሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ ገለጹ።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሰላም ማስከበር ማዕከል የሁርሶ የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለ2ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን መሠረታዊ የሠራዊት አባላት ዛሬ አስመርቋል።

በዚሁ ጊዜ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ እንዳስታወቁት ፤ሠራዊቱ የአገሪቱን ዳር ድንበርና ሉአላዊነት ለመጠበቅና ለማስከበር አንድነቱን አጠናክሮ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

“የአገሪቱ የብልፅግና ጉዞ እና የዜጎች ሰላምና ደህንነት ያልተዋጠለት የህወሓት ሽብርተኛ ቡድን በተናጠል እና ከውጭ ጠላቶች ጋር በመቀናጀት ኢትዮጵያን ለመበተን የሚያደርገው የሽብር ተግባር መቼም ቢሆን አይሳካም” ብለዋል።

“ወጣቶቹም የዚህ ታሪካዊና የሽብርተኛውን ቡድን የአገር ማፍረስ የሞት ሽረት ተልዕኮ እልባት የመስጠትና ሉአላዊነትን የማስከበር ዘመቻ አካል መሆናቸው ያኮራል” ብለዋል።

በሃገር መከላከያ ሚኒስቴር የሰላም ማስከበር ማዕከል የሁርሶ ኮንቲንጀንት ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ ኮሎኔል አዲሱ ተርፋሳ “ተመራቂዎቹ ዘመኑን የሚመጥን የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ትምህርት ጨብጠው ለየትኛውም ግዳጅ ብቁ ሆነዋል” ብለዋል።

6ተኛው አገርአቀፍ ምርጫና የህዳሴው ግድብ 2ተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በድል በተጠናቀቀበት ማግስት በመመረቅ ታሪክ የተጋሩት መሠረታዊ ወታደሮች አገርና ህዝብን የካደው የህወሓት ጁንታ ለመደምሰስ ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ የመከላከያ ሠራዊት የአገርና የህዝብ ኩራት መሆኑን ተናግረዋል ።

“ሠራዊቱ ለአገር ሉአላዊነትና ለዜጎች ደህንነት መረጋገጥ የሚከፍለው መስዋዕትነት ምንግዜም ክብር ይገባዋል” ያሉት ምክትል ከንቲባው በተለይ ሽብርተኛውን የህወሓት ጁንታ ለማስወገድ ለሚካሄደው ዘመቻ ስኬት የድሬዳዋ አስተዳደር እና ህዝብ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የትምህርት ቤቱ አሰልጣኝ መቶ አለቃ ካሊድ ዩሱፍ 'ተመራቂ ትንታግ ወታደሮች' የአገርን ዳር ድንበር የመጠበቅ ብቃታቸው ልዩና የፀና መሆኑን ተናግረዋል ።

“ደጀን በመሆንና በመቀናጀት የአገርን ሉአላዊነት ለማስከበር ፣ሽብርተኛውን የህወሓት ጁንታ ለመደምሰስና የውጭ ጠላቶችን ለመከላከል በቁርጠኝነት ይሰራሉ” ብለዋል።

ሠራዊቱ አሁን ያለው ብቃት እና ዝግጁነት ለየትኛውም የውስጥና የውጭ ጠላት መፍትሄ ለመስጠት በሚያስችለው ቁመና ላይ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በትምህርት ቤቱ የ3ተኛ ብርጌድ 3ተኛ ሻለቃ ምክትል አዛዥ ሻለቃ ሽፈራው ሽብሩ ናቸው።

“ከዛሬ ተመራቂ መሠረታዊ ወታደሮች መካከል ወታደር ወጣት ጫላ ኑር ለአገሬ ደህንነትና ሉአላዊነት የትኛውንም መስዋዕትነት ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ” ብሏል።

ለዚህም የወሰደው ስልጠና በወታደራዊ ሙያ በቂ አቅም እንዲኖረው ያገዘው በመሆኑ ይሄንኑ በተግባር እንደሚፈጽመው አስረድቷል።

ሌላዋ ተመራቂ ወታደር መድኃኒት አሰፋ በበኩሏ “የህዳሴ ግድብ 2ተኛ ዙር የዉሃ ሙሌት በተጠናቀቀበት ማግስት የተመረቅን ወታደሮች ታሪካዊነቱን በመስዋዕትነት ለማጀብ ተዘጋጅተናል” ብላለች።

በሁሉም ዘርፍ ሃገር በአሸናፊነት እንድትቀጥል እሷና የሙያ አጋሮቿ የማይከፍሉት መስዋዕትነት እንደማይኖርም ጠቁማለች።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ጀነራሎችና ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ጨምሮ የተለያዩ የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም