ከጅማ ዞን ሕዝብ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የእርድ እንስሳት በስጦታ ተለገሰ

68

ደሴ፤ ሐምሌ 17/2013(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የጅማ ዞን ሕዝብ ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና ለሌላው የጸጥታ ሃይል 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ሰንጋዎችንና በጎች በስጦታ ተለገሰ፡፡ 

ከዞኑ ሕዝብ የተሰባሰቡ 169 ሰንጋዎችንና 40 በጎችን  በወልዲያና አካባቢው ለተሰማሩ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች የሚውል መሆኑን የጅማ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቲጃኔ መሐመድ ለኢዜአ ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሓት ሀገር ለማፍረስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የዞኑ ሕዝብ ለመመከት ሁለንተናዊ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የውስጥና የውጭ ፈተናዎች በጋራ ለማለፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ እያደረገ ያለውን ጥረት ያደነቁት ኃላፊው፤ የዞኑ አስተዳደርም ህብረተሰቡን በማስተባበር ድርሻውን ለመወጣት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ዞኑ የሀገርን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር የሰው ኃይል፣የቁሳቁስና የሐሳብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ፣ድጋፉ ከ21 ወረዳዎች ሕዝብ የተዋጣ መሆኑን አመልክተዋል።

አሸባሪው ቡድን እስኪደመሰስ ድረስ ሁለንተናዊ ድጋፉ እንደሚጠናከርም አስታውቀዋል።

በጅማ ዞን የዴዶ ወረዳ አስተዳደርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፉ ናስር በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያን ከውስጥና የውጭ ጠላቶች ታድገን የበለፀገች ለማድረግ አንድነትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ወረዳው የአሸባሪውን ቡድን ሴራ ለማክሸፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ የድርሻውን ለመወጣት ሕዝቡን በማስተባበር የተዋጣ ከ300 ሺህ ብር በላይ ለሰራዊቱና ለፀጥታ ሃይሉ ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።

ጦርነቱ በድል እስከሚጠናቀቅ ድጋፉን እንደሚቀጥል የገለጹት ኃላፊው፤ የኢትዮጵያ የአንድነት፤ የፍቅርና የሰላም ተምሳሌት ባህልና እሴት እናስቀጥላለን ብለዋል።

የኢሊባቡርና ቡኖ በደሌ ዞኖችም በተመሳሳይ ሁኔታ ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና ለጸጥታ ሃይሎች ድጋፍ ማድረጋቸውም ተመልክቷል።

 የሦስቱም ዞኖች ድጋፍ ዛሬ  በወልድያ ለመከላከያ ሰራዊትና የጸጥታ ሀይሉ  ርክክብ  

እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም